
የሰላም በሮች ከተከፈቱ እና የሰላም እጆች ከተዘረጉ ሰነባብተዋል። አሁንም የመንግሥት የሰላም እጆች አልታጠፉም።
የሰላም ድምጾችም እየተጣሩ ነው። “ኑ” እያሉ ጥሪያቸውን በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ። በዚህም ሕዝብን እና መንግሥትን እንክሳለን፤ ሀገርንም እናስቀጥላለን የሚል ጽኑ ውሳኔ ላይ የደረሱ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የአማራ ክልል ዘርፈ-ብዙ ጉዳቶች ገጥመውታል። በተለይም የጦር መሳሪያ ድምጽ የሕጻናትን ሥነ ልቦና እንዲጎዳ ማድረጉ፤ የማኅበረሰቡን ዕለታዊ እንቅስቃሴ ማስተጓጎል እና ለኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት ኾኗል። ይህንን የሀገር እና የሕዝብ ችግር የተረዱ የቀድሞ ታጣቂዎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን ቀጥለዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም አማራጭን የተከተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የማኅበረሰቡን ጥያቄ ለማስመለስ ብለው በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ በመግባት በሕዝቡ ላይ ይፈጽሙት ለነበረው የበደል ድርጊት ከፍተኛ ጸጸት እንደሚሰማቸው ነግረውናል። ይህም የሕሊና ባለዕዳ እና እረፍት የነሳቸው መኾኑን ነው የገለጹት። “ከሕዝብ ወጥተን ሕዝብን መበደል እና ማሰቃየት ነውር ተግባር ነበር” ሲሉም ያለፈውን ስህተታቸውን አስታውሰዋል።
መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበላቸው ለአካባቢያቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለማኅበረሰቡ ትልቅ እፎይታ መስጠት መቻላቸውንም ተናግረዋል። የተሃድሶ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። መንግሥት ባመቻቸላቸው የሥራ ዕድል በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ነው የገለጹት። የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ እንደኾነም አንስተዋል።
አንዳንዶቹም ወደ ቀድሞ መደበኛ የመንግሥት ሥራቸው በመመለስ ሕዝብን እና መንግሥትን በቅንነት እያገለገሉ ይገኛሉ ብለዋል። “በወቅቱ ሕዝብን በድለናል፣ አሁን ደግሞ በቅን አገልግሎት እንክሳለን” ነው ያሉት።
በጫካ ያለው ሕይወት ውጣ ውረድ የበዛበት እና ሰላምን የሚያሳጣ መኾኑን ያስረዱት የቀድሞ ታጣቂዎቹ ሌሎችም በጫካ ኾነው የሕዝብን ሰላም ከመንሳት ወጥተው የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመቀበል የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ወንድማዊ ሃሳባቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ የመንግሥት ምሥረታ ወቅት ባደረጉት ንግግር በክልሉ ላለፉት ዓመታት የተወሰደው ትልቅ ትምህርት በግጭት እና በጠላትነት አሸናፊ አካል አለመኖሩን ነው ብለዋል።
ግጭት ተስፋን የሚያጨልም፣ የዕድገት ለውጦችን የሚያከሽፍ፤ የክልሉን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሚያፈርስ መኾኑንም ተናግረዋል።
መሣሪያ አንስተው በጫካ የሚገኙ አካላት የሕዝቡን ሰላም በማስቅደም የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ነው መልዕክት ያስተላለፉት።
ሀገርን እና ሕዝብን አሳልፎ ለጠላት መስጠት እና ለዳግም ጥፋት መሥራት የታሪክ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነውም ብለዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_06_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
