“የሴት ልጅን መብት ማስጠበቅ የዛሬ ኀላፊነት ነው ” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

10

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ9ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴት ልጆች ቀን የአማራ ክልል ክልላዊ ማጠቃለያ ክብረ በዓል “የታዳጊ ሴት ልጆች ሕልም፤ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ ዝግጅቶች በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) መድረኩ ከበዓል ማክበር ባለፈ ስለ ሴት ልጆች መብት፣ ደኅንነት፣ ክብር፣ የነገ ሕይወት የመንግሥት እና የማኅበረሰቡን የጋራ ኀላፊነት ለማደስ እና የተቀናጀ ቁርጠኝነት ለመያዝ ያለመ እንደኾነ ገልጸዋል። የሴት ልጅን መብት ማስጠበቅ የዛሬ ኀላፊነት ነው ብለዋል። ሴት ልጅ ላይ በእድገቷ፣ በትምህርቷ እና በጤናዋ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ለነገዋ ሀገር የሚጣል ጠንካራ መሠረት እንደኾነ ነው የገለጹት።

የልጅነት ጋብቻ የታዳጊዎችን ዕድገት የሚያደናቅፍ ከባድ እንቅፋት በመኾኑም ሕግን ከመተግበር ባሻገር የማኅበረሰብ ግንዛቤን ማሳደግ፣ ሴት ልጆችን በትምህርት ማቆየት እና ተጋላጭ ልጆችን ቅድሚያ ለይቶ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። “ታዳጊዎች የራሳቸውን ቀይ መስመር በማስመር ግባቸውን አቅደው በጽናት እንዲታገሉ፣ ችግሮች ሲያጋጥሟቸውም ለሚያምኗቸው ሰዎች እና ተቋማት ጥቆማ እና እገዛ እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ታዳጊ ሴት ልጆች የነገ ተስፋዎች ብቻ ሳይኾኑ የዛሬው ማኅበረሰብ አባላት፣ መሪዎች እና ለውጥ አምጪዎች መኾናቸውን አብራርተዋል። ልጃገረዶችን ማብቃት የሀገርን እድገት እና ሰላም መገንባት መኾኑንም ጠቁመዋል።

የልጅነት ጋብቻን፣ ጥቃትን እና መድሎን ለማስወገድ የመንግሥት፣ የወላጆች፣ የመምህራን፣ የፍትሕ እና የጤና ተቋማት የተቀናጀ ርብርብ ወሳኝ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የታዳጊ ሴቶች ቀን መከበር ሴቶች ልዩ ልዩ ችሎታ እንዳላቸው ለማስገንዘብ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሴቶች የሚሰጠው አመለካከት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስች መኾኑን የነገሩን ደግሞ የዓሉ ተሳታፊ ታዳጊ ሴቶች ናቸው።

በመድረኩ በ2018 ዓ.ም በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ ሴት ታዳጊ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የገንዘብ፣ የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_06_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleግብርናን ከኢንዱስትሪ፤ ከተማን ከገጠር የሚያስተሳስሩት ፋብሪካዎች በደብረ ማርቆስ!
Next article“ከሕሊና ባለዕዳነት ወደ ሥራ ተመልሰናል” የቀድሞ ታጣቂዎች