የጥፋት ጥምረት ውድቀት እና የኢትዮጵያ የጽናት ከፍታ

17
ታሪክ ምስክር ነው፤ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በውጭ ጠላቶቿ እና በውስጥ ባንዳዎች የተተከለባትን የመከራ እሾህ፤ የተረጨባትን የተንኮል መርዝ እና የተጸነሰባትን የጥፋት ሴራ ሁሉ በልጆቿ ደም እና አጥንት፣ በሕዝቦቿ የማይበገር አንድነት እያከሸፈች እና እያሸነፈች የመጣች ታላቅ ሀገር ናት።
ዛሬም ቢኾን የውጭ ጠላቶች በሚጎስሙት የጦርነት ነጋሪት እና የውስጥ ቅጥረኞች በሚያሰሙት ከንቱ ቀረርቶ ሳትበገር የጀመረችውን የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ በጽናት ቀጥላለች፤ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷንም በአስተማማኝ ከፍታ ላይ አቁማለች።
👉 የውጭ ባዳዎች እና የውስጥ ባንዳዎች የተሳሰረ የጥፋት መረብ፦የኢትዮጵያን ታሪካዊ ግርማ ሞገስ እና ዘመናዊ የሕዳሴ ጉዞ ለማደናቀፍ በሚደረገው ጥረት የውጭ የታሪካዊ ጠላቶች ፍላጎት እና የውስጥ የከዳተኞች ስብስብ ጥቅማቸው እንዳይቋረጥ አደገኛ የጥፋት ጥምረት ፈጥረዋል።
በተለይም ግብፅ የዓባይን ውኃ እና የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ሽፋን በማድረግ ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ራሷን የቻለች ሀገር ኾና እንዳትወጣ በዓለም አቀፍ እና በአሕጉራዊ መድረኮች ያልተቆጠበ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ጫና ስታደርግ ቆይታለች።
ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት እና አለመረጋጋት ለማዳከም ተልዕኮዋን ያስፈጽሙልኛል ለምትላቸው ኃይሎች ለዘመናት የገንዘብ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ስታቀርብ ኖራለች፤ ግብጽ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እና ቀጣናዊ ከፍታ እንደ ስጋት የመመልከት የምቀኝነት ባህሪዋ ዛሬም አልተገታም።በሌላ በኩል የሀገርን ምስጢር እና ብሔራዊ ጥቅም ለውጭ ጠላቶች አሳልፈው በመስጠት የከዳተኝነት ሚናቸውን የሚጫወቱት የውስጥ ኃይሎች በየጊዜው የግጭት እሳት በማንደድ እና የሕዝብን ሰላም በማናጋት የውጭ ጠላቶች ፍላጎት እንዲሳካ ደጅ ሲጠኑ ይስተዋላሉ።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቾ ከኾኑት ግብጽ እና ሻቢያ ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ የፈጸሙት ሕወሃት፣ ተላላኪ የውስጥ ባንዳዎች እና ግብረአበሮች ያለረፍት እየሠሩ ይገኛሉ።
ነገር ግን ይህ የባዳዎች እና የባንዳዎች የጥፋት ስብስብ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናት እና በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የማይናወጥ ተጋድሎ በየጊዜው ዕቅዱ እየከሸፈ፣ ጥምረቱም እንደ ጉም እየበነነ ይገኛል።
👉 አስተማማኙ የኢትዮጵያ የመመከት እና የመከላከል አቅም፦ዛሬ ኢትዮጵያ የትኛውንም ዓይነት ሀገራዊ አደጋ እና የጠላት ሴራ በጥበብ እና በኃይል ማክሸፍ የሚያስችል ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ገንብታለች።የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ ትጥቅ፣ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ እና በሠለጠነ የሰው ኃይል ራሱን አደራጅቶ የሀገርን ሕልውና በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ ይገኛል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ጥቅም አትመኝም፤ የማንንም ሉዓላዊነት አትዳፈርም፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ሊደፍር የሚመጣን ማንኛውንም የውጭም ኾነ የውስጥ ጠላት አትደራደርም” ብለዋል።ኢትዮጵያ የመመከት እና የማጥቃት አቅሟ በምንም መስፈርት የሚጠራጠር አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂም ቢኾን ራሷን ለመከላከል እና ጠላቶቿን አንገት ለማስደፋት ሙሉ አቅም እንዳላት አረጋግጠዋል።
የታሪካዊ ጠላቶች እና የውስጥ ከዳተኞች ሴራ የቱንም ያህል የረቀቀ ቢመስልም ከኢትዮጵያውያን የጸና አንድነት እና ከሠራዊቱ የብረት ክንድ በላይ ሊኾን አይችልም። ኢትዮጵያ የተደገሰላትን የጥፋት ድግስ ሁሉ በድል እየበጠሰች፣ በክብር፣ በኩራት እና በከፍታ ለዘላለም ትኖራለች!
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ – ጀማ ወንዝ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ።
Next articleግብርናን ከኢንዱስትሪ፤ ከተማን ከገጠር የሚያስተሳስሩት ፋብሪካዎች በደብረ ማርቆስ!