የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ – ጀማ ወንዝ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ።

3
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ የሚገኘው የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ – ጀማ ወንዝ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ የግንባታ ፕሮጀክት ሥራ ተጀምሯል።
20 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ የሚሸፍነው የመንገድ ፕሮጀክቱን ሥራ በኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የሥራ ተቋራጭነት እንደሚከናወን ተገልጿል።
የጥራት ቁጥጥር እና የማማከር ሥራውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በኃላፊነት ይከታተለዋል ተብሏል። ፕሮጀክቱ በኮንትራት ውሉ መሰረት በ14 ወራት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የለሚ-ዓለም ከተማ -ደጎሎ የመንገድ ፕሮጀክት አካል በመኾኑ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር አይነተኛ ጠቀሜታ አለው ተብሏል።
ከዚህም ባለፈ ለለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋነኛ ጥሬ ዕቃ የኾኑትን የኖራ ድንጋይ እና ጂፕሰም በከፍተኛ ፍጥነት እና ቅልጥፍና ለማጓጓዝ ያስችላል።
በለሚ ከተማ ዙሪያ እና በደብረ ብርሃን ከተማ ለተገነቡ ፋብሪካዎች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማቅረብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ነው የተባለው።
የመንገዱ የጎን ስፋት በቀበሌ መቀመጫዎች 12 ሜትር ይኾናል። በገጠር አካባቢዎች ደግሞ ከ8 እስከ 10 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ ይገነባል።
ለኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እና የበጀት ገደብ ውስጥ በጥራት እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው ሁሉ ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሀገር የማፍረስ ሴራው በሠራዊቱ ብርቱ ክንድ ተቀጥቷል!