ሀገር የማፍረስ ሴራው በሠራዊቱ ብርቱ ክንድ ተቀጥቷል!

7
የታሪካዊ ጠላትን ዓላማ የሰነቁ፣ የራሳቸውን የሥልጣን ጥም ለማርካት የፈለጉ ታጣቂዎች የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የሕዝቡን አብሮ የመኖር እሴት ለማጥፋት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።ኢትዮጵያዊነት እና አብሮነት ድር እና ማግ መኾኑን የሚያውቁት የጥፋት ኃይሎቹ በሕዝቡ መካከል ዘረኝነትን፣ መገዳደልን እና ከባሕላዊ እሴቶች ያፈነገጡ ተግባራትን በመፈጸም የማኅበረሰቡን አብሮነት ለመሸርሸር እየሠሩ ይገኛሉ።
የማኅበረሰቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄን እንደ ትጥቅ ትግል መነሻ አድርገናል ሲሉ የሚደመጡት ታጣቂዎቹ መዳረሻቸው ግን እታገልልሃለሁ ያሉትን ሕዝብ ማገት፣ መግደል እና ማሰቃየት ነው።
የጥፋት ሴራቸውን ለማሥፈጸም በሚፈጥሩት ግጭት የበርካታ ንጹሐንን ሕይወት ይቀጥፋሉ፣ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዲፈጠር እያደረጉ ነው።
የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ፍላጎት ለማሥፈጸም የሚጥሩ የሥልጣን ጥመኞች ኢትዮጵያ ጽኑ ጠባቂ እንዳላት ይዘነጋሉ። ሀገር የማፍረስ ዓላማ ይዘው በኢትዮጵያ ላይ ክንዳቸውን ያነሱ ታጣቂዎች በሀገር መከላከያ ሠራዊት ብርቱ ክንድ ተቀጥተዋል።
ከሴራቸው ቀድሞ በመገኘት በአስደናቂ ጀግንነት መውጫ ቀዳዳ አሳጥቷቸዋል። በገቡበት ገብቶ፣ ባደሩበት አድሮ የጥፋት ሴራቸውን ከምንጩ ለማጥፋት ከፍተኛ ተጋድሎን አድርጓል።
ብርቱ ክንዱን እና ድል አድራጊነቱን መቋቋም ያቃታቸው የታጣቂ ኃይሎች ገና በሩቅ ይፈሩታል። ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም እና አንድነት ዘብ የቆመው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ የተሸከሙ ባንዳዎችን በመቅጣት የሀገርን አንድነት አጽንቷል።
ከዘመኑ ጋር ዘምኖ፣ ቴክኖሎጂ ተላብሶ ግዳጅ የመፈጸም አቅሙን አይደፈሬ ያደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የውስጥ ባንዳዎች ላይ ጠንካራ እርምጃን በመውሰድ አንገታቸውን አስደፍቷል። ሁልጊዜም በጽናት በመቆም ለሀገሩ ዘብ ኾኗል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ታሪካዊ እና ወቅታዊ ጠላቶቻችን ሀገራችንን ከምሥራቅ አፍሪካ ካርታ ለማጥፋት ለዘመናት ቢሞክሩም አልቻሉም ብለዋል።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን ራሳቸው ሊመጡ ቢሞክሩ ኢትዮጵያን አይችሏትም ነው ያሉት። እንደማይችሏት አውቀው በእጅ አዙር መዋጋትን በመምረጥ በራሳችን በውስጥ በባንዳዎች እየሞከሩን ነው ብለዋል።
ምክንያት እየደረደሩ ጫካ የገቡ ባንዳዎች የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት ለማሥፈጸም፣ ሀገራቸውን ለማዳከም፣ ለማፍረስ እና አደጋ ላይ ለመጣል እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
ተላላኪ የውስጥ ባንዳዎችን አስቀድሞ መስበር ወሳኝ ወቅታዊ ግዳጅ መኾኑን አንስተዋል። መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ምሽግ እና መከታ መኾኑን ገልጸዋል።
ከሁሉም ነገር በፊት ሀገር ይቀድማል፣ ሀገር እናቆያለን፣ ለቀጣዩ ትውልድ በመስዋዕትነት እናወርሳለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የኢፌዴሪ መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚያጸና ውሳኔ ወስኗል።
Next articleየለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ – ጀማ ወንዝ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ።