
ፈተናዎች ጠንካራ ክንድን ፈጥረውለታል፤ ችግሮች ተልዕኮ የመፈጸም አቅሙን አይበገሬ አድርገውታል፣ ጠላቶች ኃያል ጥቃቱን መቋቋም አቅቷቸው በሩቅ ይሸሹታል፤ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ለዘመናት በጽናት ቆሟል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት።
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ በውስጥ ግጭቶች ያልተበገረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እያደር እንደ ወርቅ የጠራ ድልን እየተጎናጸፈ ይገኛል።
የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመኾን የሀገርን ሉዓላዊነት ለማፍረስ ቢጥሩም የክፋት ሴራቸውን በማክሸፍ እና አቅማቸውን በማዳከም ረገድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ እርምጃን ወስዷል።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በቡድን በመታጠቅ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላት ዓላማ ለማሳካት የሚጥሩ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ቅጣት በመውሰድ የሀገርን ሰላም ለማጽናት ዘወትር እየተጋ ይገኛል።
ሰላምን ለማጽናት፣ የሀገርን ዳር ድንበር እና ክብሯን ለማስጠበቅ ዘወትር በጽናት ይቆማል። የበረሃው ሀሩር፣ የደጋው ውርጭ፣ የሌሊቱ ግርማ ያልበገረው ሠራዊቱ በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ የሀገርን ሉዓላዊነት እያስቀጠለ ይገኛል።
የሰው አልባ ድሮኖችን፣ ጀቶችን፣ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ታንኮችን እና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀው፤ በድል ላይ ተመሥርቶ በድል ላይ የጸናው ሠራዊት ዛሬም በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።
ከሀገር አልፎ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም ግንባር ቀደም ደራሽ የኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ቴክኖሎጂዎችን ከመግዛት ወደ ማምረት በመሸጋገር የአፍሪካ ኩራት እየኾነ መጥቷል።
የዘመናዊ የጦር ሳይንስ እና ስትራቴጂካዊ አደረጃጀትን በመተግበር የምድር፣ የአየር፣ የባሕር ኃይል እና የሣይበር ደኅንነት ዘርፎችን በማጠናከር ግዳጅ የመፈጸም አቅሙ አይበገሬ አድርጓል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በመረጃ መረብ ማሠባሠቢያ የትንተና ዘዴዎች፤ በኤሌክትሮኒክ ውጊያ እና ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ተልዕኮን በብቃት የመወጣት አቅሙን አሳድጓል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሠንደቅ ዓላማ አከባበር ቀን ባስተላለፉት መልዕክት የጸጥታ ኃይሎች የሀገር አለኝታ፣ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና እና የሉዓላዊነታችን ታማኝ ጠባቂዎቻችን ናችሁ ብለዋል።
ለተከበረው ሠንደቅ ዓላማ በበረሃ እና በዱር፣ በውርጭ እና በሀሩር ሀገርን ከውስጥ እና ከውጭ አደጋ ለመጠበቅ የምትከፍሉት መስዋዕትነት በትውልዱ ሁሉ ከበሬታ እና ሞገስን ያገኛል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
