ባሕር በር – የመብት፣ የሕልውና እና የዜግነት ክብር ጉዳይ ነው።

9
⚓
የባሕር በር ጥያቄ ከፖለቲካዊ ድርድር እና ከጂኦፖለቲካዊ ስትራቴጂ ፍላጎት ወጣ ብሎ የአንድን ሕዝብ መሠረታዊ የህልውና መብት እና የዜግነት ክብር የሚወስን የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ነው።
ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የውኃ እና የሉዓላዊነት ጥያቄ ከዲፕሎማሲ እና ከጂኦፖለቲካዊ ስልት በላይ የቁስ አካል ፍላጎት አይደለም፤ በ100 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በታሪክ የተቸራቸውን የተፈጥሮ ጸጋ እና የሉዓላዊነት ክብር መልሶ የማረጋገጥ የዜግነት ጉዳይ እንጂ።
ያለ ባሕር በር መኖር የንግድ መስመርን በማናጋት እና የዕጣ ፈንታ ውሳኔ በሌሎች እጅ ሲወድቅ ከሰብዓዊ እና ከዜግነት መብት ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ኢኮኖሚያዊ ገመና ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የልማት ቸርነት ሳይኾን ዜጎች ዓለምን የማግኘት እና በንግድ ውድድር ፍትሐዊ ተጠቃሚ የመኾን መሠረታዊ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት መብታቸው ነው።
የባሕር በር ማጣት የንግድ ወጪን በማራዘም የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያጥፍ እና ሉዓላዊነትን ለውጭ ግፊት እንደሚያጋልጥ ሁሉ ለባሕር በር የሚነሳው ጥያቄም የዜግነት ክብሩን ሙሉ የሚያደርግ እና የኢኮኖሚ ነጻነትን የሚያጎናጽፍ ታሪካዊ የዕድል መስመር ነው።
ኢትዮጵያ በታላላቅ ወንዞች እና በሰፊ መሬት ታጅባ ያለ ባሕር በር መቆየቷ የጂኦፖለቲካዊ ስንጥቅ ውጤት በመኾኑ ይህንን በሰላም እና በጋራ ጥቅም ለመጠገን የሚደረግ ጥረት የዜጎችን የኢኮኖሚ ትንፋሽ በመክፈት የዜግነት ኩራት ከፍ የሚያደርግ ልማት ነው።
የባሕር በር ጥያቄ የጊዜያዊ ፖለቲካ አጀንዳ ሳይኾን ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው ኩራት ተሰምቷቸው ከዓለም ጋር እንዲተዋወቁ እና የሀገራቸውን ሉዓላዊነት እና የኢኮኖሚ ደኅንነት በዘላቂነት አስጠብቀው እንዲኖሩ ዋስትና የሚሰጥ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብት አላት” እንዳሉት ጥያቄው የዜግነት፣ የሕልውና እና የፍትሕ ነው።
ኢትዮጵያ በሰላማዊ ዲፕሎማሲ፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በጽናት ያንን የዜግነት መብት ታረጋግጣለች፤ ይህም የነገዋን የበለጸገች እና የከበረች ኢትዮጵያ ምሰሶ ኾኖ ይኖራል።
✍️ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበምርምር እና በዕውቀት የሚመራው የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ማስከበር የብቃት ማዕከል።