
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ለዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የሚሰማሩ ወታደራዊ፣ ፖሊስ እና ሲቪል ባለሙያዎችን ለማሠልጠን የሰላም ድጋፍ ማሠልጠኛ ማዕከልን በላቀ አቅም በ”ሰላም ማስከበር ማዕከል” ደረጃ አደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወሳል።
ማዕከሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በምሥራቅ አፍሪካ አስጠባቂ ኀይል ሥር ለሚሰማሩ የሰላም አስከባሪዎች ሥልጠናዎችን በመስጠት ለአፍሪካ ቀንድ በምርምር እና በዕውቀት የሚመራ የቀጣናው የብቃት ማዕከል የመኾን ትልቅ ዓላማ አለው።
በመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኀላፊ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ሠራዊቱ ለቀጣናው ሰላም እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተሳትፎ የረጅም ጊዜና ስኬታማ ልምድ አላት ብለዋል። ይህንን ታሪካዊ ልምድ አሁን ካለው ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ጋር አብሮ ለማራመድ ማዕከሉ ተገንብቶ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ የራሱን ልጆች ብቻ ሳይኾን የሌሎች አጋር ወንድም ሀገራትንም የጋራ አቅም እና ተሞክሮ በማዳበር ለዓለም አቀፍ ሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
አንድ ሠራዊት ሲገነባ የራሱ የኾነ ፍላጎት አለው ያሉት ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ የእኛ ሠራዊት ግንባታ ፍላጎቱ የሀገርን እና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም ነው ብለዋል። ለዚህም ሠራዊቱ በሚሰማራባቸው ሀገራት የሚገጥሙትን የግጭት መነሻዎች በሳይንሳዊ መንገድ የሚመረምር፣ ችግሩን በውል የሚያነብ፣ የሚያውቅ እና እንደየሁኔታው አቅዶ ሊመራ የሚችል ብቁ አመራር ለማፍራት ከፍተኛ ጊዜ ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ዘመኑ የትብብር መኾኑን የጠቀሱት ኀላፊው ለሀገራችን ሰላም እንደምናስበው ሁሉ በጎረቤቶቻችንም ሰላም መኖሩ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። የድንበር ተሻጋሪ ሰላምን ለማረጋገጥ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ጎረቤት ሀገራትም እንደእኛ የሰላምን አስፈላጊነት ተረድተው በጋራ እና በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
ማዕከሉ ባለው የኮንቲጀንት ማሠልጠኛ አማካኝነት ወደ ግዳጅ የሚሰማራው ኀይል በሙሉ የጋራ አስተሳሰብ እና አረዳድ ኖሮት እንዲሄድ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል። ለዚህም ሠራዊቱ ከሚሄድበት ሀገር ተጨባጭ ባህሪ፣ የአየር ጠባይ፣ ባሕል እና ወግ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ሕጎች ጋር የተናበበ ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር የጋራ የሥራ ቋንቋ እንዲኖረው እና በቢሮ አሥተዳደር በተለያዩ እርከኖች ያሉ ሠራተኞችን ብቃት ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ገልጸዋል።
ማዕከሉ በሰላም እና ግጭት አፈታት ዙሪያ በምርምር እና በዕውቀት የሚመራ ኀይል ለማፍራት በጀመረው የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ውጤታማ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
