‎ ባሕር ዳር የተፈጥሮ እና የከተሜነት ዘላለማዊ ውህደት ማሳያ

8

‎🌊 ባሕር ዳር የተፈጥሮ እና የከተሜነት ዘላለማዊ ውህደት ማሳያ 🌴 🏙️

‎የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የጣና ሐይቅን እና የከተማዋን ውህደት ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

ከዚህ ቀደም ወደ ከተማዋ የሚገባ ማንኛውም መንገደኛ ጣናን በቅርበት ለማየት የተወሰኑ ስፍራዎችን መፈለግ ወይም ርቆ መሄድ ግድ ይለው ነበር። የኮሪደር ልማቱ ግን ይህንን ግርዶሽ ሙሉ በሙሉ በመግፈፍ ጣናን የከተማዋ ቀዳሚ የፊት ገጽታ አድርጎ በጉልህ አውጥቶታል።

‎ኮሪደሩ ተፈጥሮን ከዘመናዊ ከተሜነት ጋር በሚያስደንቅ ሁኔታ አዋህዷል። ይህም ሐይቁ ከከተማዋ ዳርቻ የሚገኝ የውኃ አካል ብቻ ሳይኾን የባሕር ዳር እውነተኛ ማንነት መኾኑን አሳይቷል።

‎የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኮሪደር ልማት ሥራው ሐይቁ ለከተማው ነዋሪዎች፣ ለቱሪስቶች እና ለማንኛውም መንገደኛ በግልጽ እንዲታይ ማድረጉን አረጋግጠዋል። ከዚህም ባሻገር ምቹ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራ እና የከተማ ዋነኛ የውበት መገለጫ መኾኑን አስታውቀዋል።

‎የኮሪደር ልማቱ የጣና ሐይቅን ገጽታ በጉልህ ሊገልጥ የቻለው ከዚህ ቀደም ለዕይታ ማነቆ የነበሩ ግርዶሾችን፣ አጥሮችን እና ያልተደራጁ ሰፈሮችን ሙሉ በሙሉ በማስተካከል እና የከተማዋን ዋና ዋና ጎዳናዎች በቀጥታ ከሐይቁ ጋር በማስተሳሰር ነው።

‎በአሁኑ ወቅት ሰፋፊዎቹ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ በዘንባባ ያጌጡት አረንጓዴ ስፍራዎች ወደ ሐይቁ ዳርቻ የሚያመሩት እጅግ ማራኪ በኾነ ተፈጥሯዊ ፍሰት ነው። ይህም መንገደኛው ሳያስበው የውኃው እና የማዕበሉ ድምጽ ውስጥ ራሱን እንዲያገኝ አግዟል።

‎የዕይታ መስመሮች ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲኾኑ መደረጋቸው፣ ዘመናዊዎቹ መንገዶች ጣናን እንደ ትልቅ የተፈጥሮ ስዕል አድርገው አሳምረውታል። በዚህም የተነሳ ማንኛውም ጎብኝ ወደ ባሕር ዳር ሲገባ በቅድሚያ የሚቀበለው የሕንጻዎች ግርግር ብቻ ሳይኾን፣ አድማስ አቋራጩ እና ሰላማዊው የጣና ሐይቅ ጭምር ኾኗል።

‎የኮሪደር ልማቱ ከፈጠረው ማራኪ የዕይታ መስህብነት ባሻገር ነዋሪውም ኾነ ጎብኝው ከተፈጥሮው ጋር ጥልቅ እና የጠበቀ ቁርኝት እንዲፈጥር በር ከፍቷል። በሐይቁ ዳርቻ የተሠሩት እንደ ዘምባባ ፓርክ፣ ጣና ፓርክ፣ ሹም አቦ መናፈሻ የመሰሉ ዘመናዊ የሕዝብ መዝናኛዎች እና የእግር ጉዞ ስፍራዎች ጣናን የከተማዋ የሕዝብ መሠብሠቢያ ሳሎን አድርገዋታል።

‎ድሮ በጓሮ በኩል የተተወ ይመስል የነበረው የጣና ዳርቻ ዛሬ የባሕር ዳር የክብር ካባ ኾኗል። ይህ ዲዛይን የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር አልፎ የጣና ልጆች የሚለውን የባሕር ዳር ሕዝብ መገለጫ በተጨባጭ መሬት ላይ ያሳየ እና ተፈጥሮን ማዕከል ያደረገ የከተማ ፕላን ትልቅ ማሳያ ለመኾን በቅቷል። አሁን ላይ ማንም ሰው በነጻነት ወደ ሐይቁ ቀርቦ ንጹህ አየር እንዲተነፍስ እና የውኃውን ጸጥታ እንዲያጣጥም ምቹ ዕድል ተፈጥሮለታል።

‎የኮሪደር ልማቱ ከኮንክሪት እና ከአስፋልት መንገድ ባለፈ ከተማዋን እና የተፈጥሮ ሀብቷን በሚገባ በማስታረቅ ጣና የባሕር ዳር የጀርባ መልክ መኾኑ አብቅቶ የከተማዋ ዋነኛ መድረክ እንዲኾን አድርጎታል። ዛሬ ላይ ባሕር ዳርን መጎብኘት ማለት ጣናን መኖር፣ ጸጋዋን ማወቅ፣ ነፍስን በሀሴት መሙላት ኾኗል።

‎#አሚኮ #ጣና_ባሕርዳር #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_09_2019_ዓ_ም

‎በስማቸው አጥናፍ

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎ዛሬ አንድ ኾነን ከተራመድን የማንሻገረው ወንዝ የለም።