
የአማራ ክልል ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በ2018 በጀት ዓመት ሕዝብ መንግሥት እንዲጠናከር እና
ሰላምን አጥብቆ የፈለገበት እንደነበር ገልጸዋል።
መንግሥት እንዲጠነክር ደግሞ ምክር ቤት መጠንከር እንዳለበት ተናግረዋል። ምክር ቤቶች የጠንካራ ሕዝብ መሠረቶች ናቸው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ምክር ቤቶች በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሠሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል። በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን በተከናወነው ሥራ የሕዝብ ወኪሎች ከፍተኛ ድርሻ መወጣታቸውን አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የነበሩ ክፍተቶችን እና ጥንካሬዎችን በመለየት፣ ጉድለቶችን በመሙላት እና መልካም ጎኖችን በማስቀጠል የጋራ መግባባት ይፈጠራል ብለዋል።
በመድረኩ የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ቀርቦ የጋራ እንደሚደረግም ገልጸዋል። በክልሉ ያሉ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የአንበሳውን ድርሻ መወጣት ያለበት ምክር ቤቱ መኾኑን የተናገሩት አፈ ጉባኤዋ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድም የሕዝብን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደኾነ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት ዶክተር የሻምበል አጉማስ የሕዝብ ወኪሎች ከሕዝብ መራቅ እንደሌለባቸው አሳስበዋል። እያንዳንዱን የሕዝብ እንቅስቃሴም በቅርበት መከታተል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ሰላም ሰፍኖ፣ ማኅበራዊ እረፍት ተገኝቶ በሙሉ አቅም ወደ ልማት መግባት እንዲቻል የግጭቱ ጥንተ-ሰበቦች ላይ በግለሰብ፣ በኅብረተሰብ፣ በተቋማት፣ በሠራተኞች እና በሌሎች መካከል ተከታታይ እና የሰከነ ውይይት እንዲደረግም የሕዝብ ወኪሎች ጥረት እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።
#አሚኮ #ምክርቤት #ልማት #ሰላም #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_08_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
