
በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ በግብርናው ዘርፍ 9 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እና የሰብል ምርታማነትን በሄክታር ወደ 36 ነጥብ 7 ኩንታል ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችሉ የገጠር ኮሪደር ልማት፤ የመስኖ እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ዘመናዊ ግብርናን ለማሳደግም የትራክተር እና የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ሰፋፊ የፍራፍሬ እና የሰብል ኩታገጠሞች ይተገበራሉ ብለዋል። “መፈጸም የማይችል ዕቅድ ረብ የለውም” በሚል መርህ የመሪዎችን የመፈጸም አቅም እና የሥራ ስነ ምግባር የማጠናከር ተግባር ተጀምሯል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የመልማት አቅም ላላቸው ዞኖች የምርት ማሳደጊያ ግብዓት አቅርቦትን፣ የቴክኖሎጂ ሥርጭትን እና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በጥብቅ ክትትል እንደሚያቀርብም ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ሰፊውን ሕዝብ በማስተባበር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ድህነትን ለመቀነስ በቁርጠኝነት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።
#ደብረ_ማርቆስ #መስከረም_08_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ዘላለም አስፋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
