
የሠላም ጠሉ ሕገወጡ ህወሃት ለጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በመጥላትና ከቡድኑ ጋር ሆነው አለመዋጋትን በመምረጥ ወደ 300 የሚጠጉ የህወሃት ታጣቂዎች በተከዜ በኩል ለሚገኘው ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ እጅ መሥጠታቸውን ዕዙ አሥታውቋል።
በምዕራብ ግንባር ተከዜ አቅጣጫ ልዩ ቦታው በተከዜ ድልድይ ግራና ቀኝ አቅጣጫ ለዕዙ ሠራዊት እጅ የሠጡ የህወሃት ታጣቂዎች የኢትዮጵያና የትግራይ ሕዝብ ጠላት ሆኖ የትግራይን ሕዝብ ሲጨፈጭፍ ከነበረው ሻዕቢያ ጋር ፅምዶ በሚል እሳቤ የፈጠሩት ጥምረት ለትግራይ ሕዝብ የማይጠቅምና የሚጎዳ መሆኑን በመገንዘብ በቀጠናው ከሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ጋር ቀደም ብለው በመሠረቱት ግንኙነት በመነጋገር እና መንገድ በማመቻቸት እጅ መሥጠት እንደቻሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በጠብመንጃ ሳይሆን በመነጋገር እና በመግባባት ነው የሚል እምነት ይዘው ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሠራዊት እጅ የሠጡት የሕገወጡ ህወሃት ታጣቂዎች ከሁለት መቶ ሰማንያ በላይ የነፍሰ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ በርካታ የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ የጦር ሜዳ መነፅርና ልዩ ልዩ ዶክመንቶች ይዘው መግባታቸውንም ዕዙ አሥታውቋል።
ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ሠላማዊውን የትግራይ ሕዝብ ወጣት በማፈስ ወደ ጦርነት ለመማገድ የሚሠሩ ዘራፊ እና ወርቅ አውጪ የህወሃት አመራሮችን ፍላጎት በመቃወም እጅ የሠጡት የህወሃት ታጣቂዎች አሁንም ቢሆን አለመግባባቱ ሊፈታ የሚችለው በጥቂት ጨቋኝ የህወሃት አመራሮች ፍላጎት ሳይሆን በመነጋገር ብቻ ነው የሚል ሙሉ እምነት ይዘው እጅ መሥጠታቸውንም ተናግረዋል።
እጅ ከሰጡ የህወሃት ታጣቂዎች መካከል ከክፍለጦር አዛዥ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሻለቃና የሻምበል አመራሮች ይገኙበታል ያለው ዕዙ ይህ የሚያመላክተው ታጣቂው ሃይል ሳይፈልግ በህወሃት ሥርዓት አገዛዝ አሥገዳጅነት የሚዋጋ ኃይል ስለመሆኑ እንደሆነም ገልጿል።
ህገወጡ ህወሃት ከጦርነት አዙሪት የመውጣት ፍላጎት የሌለው ፅምዶ በሚል አካሃድ ሕዝቡን አሁንም ወደ ከፋ ችግር ውስጥ ለመክተት የሚጥር፤ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሠላም የማይመች፤ የቀረበለትን የሠላም አማራጭ የማይቀበል በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣ ሥለመሆኑም እጅ የሠጡ ታጣቂዎች ተናግረዋል።
አሁን ላይ የህወሃትን የአገዛዝ ሥርዓት በመጥላትና ሠላምን በመምረጥ እጅ ለመስጠት የሚጠባበቁ በርካታ የትግራይ ወጣቶች አሉ ያሉት ታጣቂዎቹ የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠልና ሠላም ለማሳጣት ህወሃት ወጣቱን እያስገደደ ሳይፈልግ ለጦርነት እያዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል። ተገዶ የገባው የትግራይ ወጣትም ይህን አውቆ እና ተረድቶ ጊዜና ሁኔታው ሲመቻችለት እጅ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ታጣቂዎቹ ገልፀዋል። ዘገባውን ያደረሰን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ነው
