
ዛሬ ደግሞ ጳጉሜን 5 “የነገው ቀን” እየተከበረ ነው። ይህ ቀን እና ስያሜ ከተለመደው የዘመን መለወጫ ቃላት ባለፈ ፈታኝ ሀቅን እና ተስፋን ያዘለ ነው። ከእነዚያ ጊዜያት ጀምሮ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች መውደም፣ የግብርናው ዘርፍ መስተጓጎል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ መፈናቀል እንደመጥፎ ታሪክ የሚነሱ እንጅ የማይደገሙ ናቸው።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ዕለቱ ለክልሉ ሕዝብ የሕይወት ዋስትና፣ የመረጋጋት እና ወደ መደበኛ ኑሮ የመመለስ መሠረታዊ የሰላም መሰረት ኾኖ ሊገለጽ ይችላል።
እንደ ሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበረ-ፖለቲካዊ ምልከታዎች ረጅም ጊዜ በወሰደ የትጥቅ ግጭት እና አለመረጋጋት ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ ነገን በተስፋ እና በንቃት ለመመልከት ዛሬ ላይ የጥይት ድምጽ ቆሞ የልብ መረጋጋትን ይሻል። ጳጉሜን 5 በእርግጥም የነገ ብሩህ ተስፋ የሚሰበክበት፣ በቁርጠኝነትም የሚሠራበት ሊኾን ይገባል።
የእውነተኛ ሰላም መለያ የኾነው ነገ የሚረጋገጠው በመሳሪያ አፈሙዝ ሳይኾን በቅን ልቦና፣ በእውነተኛ ፖለቲካዊ ውይይት እና ሁሉን አሳታፊ በኾነ ዘላቂ መፍትሄ ላይ ብቻ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመት መወያየት ይሻላል ያሉት። ይህም የሀሳብ የበላይነት የትኛውንም አካል ያለ ጉዳት አሸናፊ የሚያደርግ መሳሪያ መኾኑን የሚያሳይ ነው።
በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ወገኖችም የሰላምን አማራጭ በመቀበል በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ኑሮን እየኖሩ ነው። የትጥቅ ትግል ሕዝብን ከማጎሳቆል፣ ኢኮኖሚውን ከማሽመድመድ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን እና አብሮነትን ከማሻከር የዘለለ ትርጉም እንደሌለው አረጋግጠዋል።
አሁንም ለሕዝብ እና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚጨነቅ ታጣቂ ኅይል አሸናፊነትን በሰላማዊ የትግል አማራጭ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የትናንቱን የጥፋት አዙሪት በማስቆም ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባሕልን በተግባር ማሳየት ካልተቻለ የነገው ቀን ከቀን መቁጠሪያ ለውጥ የዘለለ ትርጉም አይኖረውም።
በመኾኑም የነገው ቀን የሦስት ዓመቱን የሰላም እጦት፣ የሕዝብ መከራ እና የፈረሱ እሴቶችን በቁጭት በመገምገም በክልሉ እውነተኛ እርቅ እና ሰላም ለማውረድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከልብ እንዲሠሩ የሚያስገድድ የህሊና ጥሪ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
