በልዩነት ውስጥ አንድነት፤ በኅብረት ውስጥ አብሮነት ተገምዷል።

6

 

ለዘመናት በኅብረት ቆመዋል፤ ደስታቸውን እና ሀዘናቸውን በኅብረት ተካፍለዋል፤ ለችግራቸው በጋራ መፍትሔ አስቀምጠዋል፤ ማኅበራዊ እሴታቸውን ጠብቀዋል።

አብሮነት እና መተባበርን ለማጠናከር ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በጋራ ማክበር ያዘወትራሉ ኢትዮጵያውያን። በአማራ ክልል በተለይም በክረምት ወራት ማኅበራዊ ኅብረቶች ይበልጥ ይጎላሉ። ማኅበረሰቡ በየአካባቢው የሚከበሩ በዓላትን የአንድነታቸው መገለጫ፤ የኅብረታቸው መሠረት አድርገው ቆይተዋል።

አሮጌው ዓመት ሲገባደድ፤ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ደብረ ታቦር (ቡሄ)፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ፤ ከሴ አጨዳ እና አሱሪቴ የተሰኙ የነሐሴ ወር ጸጋዎች የአማራ ሕዝብ የአብሮነት ማሳያዎች ናቸው።

በተለያዩ ወቅቶች አብሮነትታቸውን ቢያጠነክሩም በክረምት ወራት በሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ግን አንድነታቸውን አጉልተው ያሳያሉ። ለወጣት ልጆቻቸው እና ለቀጣዩ ትውልድ ኅብረትን፤ ባሕላዊ እሴትን ያስተምራሉ።

በአማራ ክልል የክረምት የአደባባይ በዓላት ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር “በዓላት የማንነት፤ የታሪክ እና የባሕላዊ እሴቶችን፤ የትውልድ ቅብብሎሽን የሚያሳዩ መንገዶች ናቸው” ብለዋል። በዓላት የኅብር መገለጫ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፤ የተለያዩ ቋንቋዎች እና ባሕላዊ ሥርዓቶች የያዘችው ኢትዮጵያ የኅብር መገለጫ ናት። ሀገራቸውን ለማሻገር፤ የኢኮኖሚ ከፍታቸውን ለማረጋገጥ፤ አብሮነታቸውን ለማጉላት እና ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተለያዩ ባሕላዊ እሴቶቻቸውን ይጠቀማሉ።

ኢትዮጵያዊያን ለኅብረታቸው ቋንቋ፤ ለአንድነታቸው ማንነት አይገድባቸውም። በልዩነታቸው ውስጥ አንድነት፤ በኅብረታቸው ውስጥ አብሮነት ለዘመናት ተጋምደው ኖረዋል።

ኅብረታቸውን በመጠቀም በዓድዋ ድል የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስከብረዋል፤ ለአፍሪካም የነጻነት ምልክት ኾነዋል። ዳግማዊ ዓድዋ በኾነው ዓባይ ግድብም ዳግም ኅብረታቸውን ለዓለም አሳይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጳጉሜን 4 የኅብር ቀንን አሥመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በሀገር በቀል እሴቶቿ፤ የነገውን ብሩህ ተስፋዋን በገዛ እጆቿ እየቀረጸች ትገኛለች ብለዋል።

በትውልድ ቅብብሎሽ የተገኙ ድንቅ የሀገር በቀል እሴቶችን በማጎልበት ለጽኑ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የማይናወጥ መሠረት ጥለናል ነው ያሉት።

#አሚኮ #የኅብር_ቀን #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_04_2018_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ የብዝኃ ማንነቶች ድምር ናት፡፡
Next articleማዕድ ማጋራት፦ ከምግብ ባሻገር ፍቅር እና ክብር