ኢትዮጵያ እና ጽናት የማይነጣጠሉ ናቸው

15
ኢትዮጵያ የዘመናት ፈተናዎችን እና ማዕበሎችን ተሻግራ በታሪክ አወንታዊ አምድ ላይ የቆመች የጽናት እና የድል ምሽግ ናት። የሀገሪቱ ታሪክ የውጪ ወራሪዎችን እና የውስጥ ችግሮችን በጋራ መንፈስ በመመከት የተገነባ የድል ማኅደር ነው። ኢትዮጵያውያን በፈተና ጊዜ አንድ ይኾናሉ፤ ፈተናዎችንም እንደ መሰላል በመጠቀም አንድነታቸውን እና ኅብረታቸውን ይበልጥ ያጠናክራሉ።
ሕዝቡ የማይበገር የሞራል ልዕልና ገንብቷል። አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሀገርን በማስቀደም የከፈሉት መስዋዕትነት የትውልድ አደራ ኾኖ ዛሬም ድረስ ተጋምዶ ቀጥሏል። በታሪክ ኢትዮጵያ በፈተናዎች ልክ ወድቃ አታውቅም። ይህም ዘመናትን የዘለቀው ገናናነቷ ከዚህ የማይናወጥ ጽናት የመነጨ ነው።
የአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔዎች ባለቤት ናት ብለዋል። ሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚገጥሟትን ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች ተቋቁማ ማንነቷን ጠብቃ ማቆየቷ የጽናት ማሳያ እንደኾነም ገልጸዋል።
​ጽናት ችግርን በቀላሉ በመላመድ ብቻ የሚታለፍ ሳይኾን፤ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ከውድቀት በመነሳት እንደገና የማንሠራራት እና ለልዕልና የመብቃት ሂደት ነውም ብለዋል። ሌሎች የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ሀገራት የገጠማቸውን ውስጣዊ እና ውጫዊ ቀውስ መቋቋም አቅቷቸው ሲጠፉ ኢትዮጵያ ግን በርካታ ፈተናዎችን አልፋ ማንነቷን አስጠብቃ መዝለቅ የቻለች ሀገር እንደኾነች ነው የተናገሩት።
ሀገሪቱ ችግሮች በከበቧት ጊዜ ሕዝቦቿ በአንድነት በመቆም አደጋዎችን መጋፈጥ ችለዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ እና የጽናት ጽንሰ-ሀሳብ የማይነጣጠሉ፤ ከታሪካዊ ቅርስ ባለፈም የሕልውና መሠረት እንደኾኑ ነው የገለጹት። ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿ በጋራ ጽናት ማንነታቸውን አስጠብቀው ዛሬ ላይ መድረሳቸው ለዚህ ዘላቂ እውነት ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል። ጽናት ማለት መከራዎችን ችሎ፤ ችግሮች ሳይበትኑት ማንነቱን እና ክብሩን ጠብቆ ለላቀ ከፍታ መብቃት ነውም ይላሉ።
የጋራ ሥነ ልቦናን እና አብሮነትን በመጠቀም ከውድቀት መነሳት፤ ማንሠራራት፣ የሀገርን ታሪካዊ ቀጣይነት ማረጋገጥ የዘመናት ሁነት ነው ብለዋል።
ወደ ቀደመ ገናና ክብሯ ለመመለስ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ይገባል ነው ያሉት። በምግብ ራስን ከመቻል ጀምሮ ጠንካራ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን መፍጠር፣ የሰላም ጥያቄዎችን በመመለስ የተረጋጋ ሀገራዊ ሁኔታን መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ይች ሀገር ዛሬም እንደ ትናንቱ የጽናት ማማ ኾና ትቀጥላለች፤ ሕዝቦቿም በታሪክ አውድ ውስጥ ሁልጊዜ አሸናፊ ኾነው ይኖራሉ ነው ያሉት።
✍️ ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleባሕልን መጠበቅ ትውልድን መቅረጽ እና ማንነትን ማስቀጠል ነው።