
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጳጉሜን ሶስት የጽናት ቀንን ምክንያት በማድረግ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያን ስናስብ፣ ሌት ተቀን በጽናት በመቆም ሀገርን ከጠላት ለመጠበቅ ወጥተው ለሚያድሩት ብርቱ የጸጥታ ኃይሎቻችን ቅድሚያ ሳንሰጥ ስለ ሁለንተናዊ ከፍታ ማሰብ ፈጽሞ አይቻልም ብለዋል።
ለዚህም ነው በዚህ የጽናት ቀን ለሀገረ መንግሥታችን ዘላቂነት እና ሉዓላዊነት ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን የከፈሉትን የጀግኖቻችንን ታሪካዊ መስዋዕትነት በከፍተኛ ሀገራዊ ክብር የምንዘክረው፡፡
ዛሬ ላይ ሀገራችን በራሷ ዕውቀትና በልጆቿ አቅም የላቀ የቴክኖሎጂ ብቃት ያላቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ዘመናዊ የታጠቁ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን፣ ከባድ መሣሪያዎችን እና መድፎችን፣ ተተኳሽ ጥይቶችን በራሷ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ችላለች ነው ያሉት።
ይህ በራስ የመቆም አቅም የሕዝባችን ሰላም እና የሁለንተናዊ ኢኮኖሚ እድገታችን ጽኑ መሠረት በመኾኑ ሀገራዊ ጽናታችንን በተጨባጭ ልማት፣ በጠንካራ የመጠበቅ እና የመከላከል አቅም እያረጋገጥን የኢትዮጵያን ዘላቂ ብልጽግና እናጸናለን ብለዋል።
