
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጳጉሜን ሁለት የማንሠራራት ቀንን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል።
በመልዕክቱ እንኳን ለጳጉሜን ሁለት የማንሠራራት ቀን አደረሳችሁ፣ አደረሰን ብሏል።
ኢትዮጵያ የብልጽግና ትልሞቿን በፅኑ መሠረት እየገነባች ነው፡፡ ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት ፖሊሲዎች እና ዕቅዶች እየተመራች ለኹለንተናዊ ብልጽግና እየተጋች ትገኛለች፡፡ በየዘመን አንጓው ያጋጠሟትን ፈተናዎች በተደመረ ዐቅም እየተሻገረች፤ ከችግሮች እና ፈተናዎች ዕድሎችን መንጭቃ እያወጣች፤ ነገዋን በጠንካራ መሠረት ላይ እያጸናች ነው፡፡
ለዘመናት የኢትዮጵያን ሠንደቅ ከዓድማስ እስከ ዓድማስ የሚያውለበልበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገውን ታሳቢ አድርጎ እንደ ቢሾፍቱ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባሉ መሠረተ ልማቶች እና ኹለንተናዊ ለውጦች ውስጥ እያለፈ ነው፡፡ ፡፡ ነባር እና ዐዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየለሙ እና ተደራሽነታቸዉ እያደገ ነው፡፡ ግብርናችን ከዝናብ ጥገኝነት እየተላቀቀ እና የገጠሩም የከተሜዉም የሥራ ዕድል እየኾነ ነው፡፡ የታዳሽ ኃይል አማራጮቻችን ከውኃ፣ ከነፋስ፣ ከፀሐይ፣ ከጂኦተርማል እና ከኑክሊየር ኃይል እንዲኾኑ የመደመር መንግሥት ሌት ተቀን እየሠራ ነው፡፡
ከተሞቿ ጎስቋላ ገጽታቸዉ እየተቀየረ እና ነገን እየዋጁ፤ መሠረተ ልማቶቿ እየተስፋፉ እና እየተቀናጁ፤ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዐቅሟ እየተጠናከረ፤ የቀጣናዉ የታዳሽ ኃይል ማዕከልነቷ እያደገ፤ የማዕድን ሀብቶቿን በላቀ ደረጃ ጥቅም ላይ እያዋለች ለመጪዉ ትውልድ ኹለንተናዊ ብለጽግና እየሠራች ነው፡፡
የኢትዮጵያን ማንሠራራት የሚያበስሩ፤ እመርታዊ ዕድገቷን የሚያፋጥኑ ፅኑ መሠረቶች ላይ እየተገነቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሥርዐቱን ለማጽናት እና መሻታቸውን እውን ለማድረግ ያላቸዉን ቁርጠኝነት በመንግሥት ጥሪዎች በሚያሳዩዋቸው ተሳትፎዎች እየገለጹ ነው፡፡
በሰባተኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ከሌሊት እስከ ሌሊት ፈተናዎችን ተቋቁመው ድምፅ መስጠታቸው እና ውጤቱን በደስታ መቀበላቸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ በየዓመቱ እያደገ የመጣ ተሳትፎ እና ስኬት ማስመዝገባቸው፤ የልዩነት ሐሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ለመግራት ሀገራዊ ምክክርን መምረጣቸው ኢትዮጵያውያን በመደመር መንግሥት ትልሞች ላይ የያዙትን የጋራ ተስፋ እና ለስኬቱም እያደረጉ ያለውን ርብርብ የሚያሳይ ነው፡፡
የዴሞክራሲ ሥርዐትን በማንበር፤ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚን በመከተል፤ የከተሞችን ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ወደ ገጠር በማላመድ፤ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በመሻሻል፤ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቱን በማዘመንና በማስፋፋት ለኢትዮጵያ ኹለንተናዊ ብልጸግና ፅኑ መሠረት እየተቀመጠ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጳጒሜን ሁለትን “የማንሠራራት ቀን” በሚል ስያሜ እያከበርን የምንገኘው፡፡
ጳጒሜን 2/ 2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ
