
ትምህርት የትውልድ መቅረጫ፣ ለሀገር እድገት እና ለዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት ዋና መሠረት ነው። ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገራችን ኢትዮጵያ የነበረው የትምህርት ዘርፍ በከፍተኛ የጥራት ውድቀት እና መዋቅራዊ ስብራት ውስጥ ይገኝ ነበር።
በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሰፈነው የኩረጃ ባሕል፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመማሪያ ትምህርት ቤቶች እና ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር ያልተጣጣመ ሥርዓተ-ትምህርት የዘርፉ ዋነኛ ማነቆዎች ነበሩ።
👉 የቀደመው ስብራት እና ዘርፉ የነበረበት ፈታኝ ሁኔታ፦
የትምህርት ዘርፉ ባለፉት ጊዜያት በቁጥር እድገት ላይ ብቻ በማተኮር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ሥረቆት እና ኩረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ስር ሰዶ ነበር። በርካታ የገጠር ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች የኾኑ፣ የላበራቶሪ፣ የቤተ-መጻሕፍት እና የቴክኖሎጂ ማዕከላት ያልተሟሉላቸውም ነበሩ።
ትምህርቱ ከሀገር በቀል ዕውቀት፤ ከኢኮኖሚው ፍላጎት እና ከዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ እድገት ጋር የተራራቀ ነበርም ማለት ይቻላል። እነዚህ ፈተናዎች ተዳምረው በትውልድ እና በሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድረዋል።
👉 የማንሠራራት ጉዞ እና የተወሰዱ መዋቅራዊ እርምጃዎች፦
ባለፉት ዓመታት ስኬታማ ውጤቶች ከተመዘገቡባቸው ዘርፎች መካከል የትምህርት ዘርፉ ቀዳሚ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል።
መንግሥት በትምህርት ዘርፉ ባደረገው ከፍተኛ የሪፎርም ሥራ የፈተና ኩረጃ እና ማጭበርበር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፤ ይህም ተማሪዎች፣ መምህራን እና ወላጆች በእውነተኛ የትምህርት ጥራት እና ውጤት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን ተናግረዋል።
ለነገዋ ኢትዮጵያ ብቁ ዜጋን ለመቅረጽ የሕጻናት አዕምሮ ዕድገት የሚጀምርበት ቅድመ-መደበኛ ትምህርት ወሳኝ ነው፤ ለዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ35 ሺህ በላይ የአጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤቶችን መገንባት ተችሏል ነው ያሉት።
በእነዚህ ተቋማት የሚማሩ ሕጻናት በቀጣዮቹ 20 ዓመታት የኢትዮጵያ እድገት እና ልማት ዋና መሠረት እንደሚኾኑ እምነታቸውን ገልጸዋል። አዲሱ ትውልድ ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እንዲራመድ ለማድረግ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና የቴክኖሎጂ ትምህርቶች እንዲስፋፉ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
መንግሥት በትምህርት ጥራት፣ በፈጠራ እና በዲጂታል ሽግግር ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱ ለዘርፉ የማንሠራራት ጅማሮ ማሳያ ነው። ይሁን እንጅ ከሀገሪቱ ፍላጎት እና ከሚጠበቀው የጥራት ደረጃ አንጻር ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅም ነበር የተናገሩት።
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ መደረጉ እና በይነ-መረብን (ኦንላይን) የተከተለ አሠራር መዘርጋቱ የፈተና ሌብነትን ማስቀረት መቻሉን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።
በ2016 በበይነ-መረብ የተጀመረው የፈተና አሰጣጥ አሁን ላይ የተፈታኝ ተማሪዎችን መጠን 62 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲኾን በቀጣይም መቶ በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል ሚኒስትሩ። ይህ እርምጃ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመገንባት ባሕል እንዲጎለብት አድርጓል ነው ያሉት።
👉 የመሠረተ ልማት እና የትምህርት ቤቶች እድሳት፦
ከሕዝብ እና ከተለያዩ አካላት በተሠበሠበ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የወደፊቱ መሪዎች እና ሳይንቲስቶች የሚወጡባቸው ሀገር አቀፍ የሞዴል እና የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሁሉም ክልሎች የመገንባት እና የማቋቋም ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
በልዩ ሁኔታ የበለጸጉ እና የጎበዙ ተማሪዎችን አቅም የሚያሳድጉ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት በተጨማሪ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግ እና ማቲማቲክስ (STEM) ማዕከላት እየተስፋፉ እንደኾነም አንስተዋል።
ተማሪዎች በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይወጡ በማድረግ የመማር ፍላጎት እና ውጤታማነትን ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።
👉 አዲስ የሥርዓተ-ትምህርት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር፦
በክህሎት፣ በፈጠራ፣ በሥነ-ምግባር እና በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ትኩረት ያደረገ አዲስ የትምህርት ፍሬምወርክ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። የሙያ እና ቴክኒክ (TVET) ዘርፉ ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር እንዲናበብ ተደርጎ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት ተጀምሯል።
👉 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ-ገዝነት፦
ዩኒቨርሲቲዎች ከፖለቲካ እና ከአካባቢያዊነት ነጻ ኾነው በምርምር እና በብቃት ላይ እንዲያተኩሩ ሕጋዊ ራስ-ገዝነት እንዲያገኙም እየተደረገ ይገኛል።
#አሚኮ #education #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_02_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
