የጊንጥ ፖለቲካ – ያሻገሩትን የመንደፍ ፍጻሜ።

5
🦂
ሕገ ወጥ እና ጽንፈኛ ቡድኖች የሕዝብ ድጋፍ ሲያጥራቸው የሌሎችን ብሶት መጠቀሚያ ያደርጋሉ። የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ሲሉ ጊዜያዊ አጋሮችን እና አጃቢዎችን ይሠበሥባሉ። የሌሎችን ቁስል በማከክ አብረዋቸው እንዲሰለፉም ያደርጋሉ። ኪሳራ ሲያጋጥማቸውም ሀገርን እስከማፍረስ ይደርሳሉ።
ይህ አይነቱ የፖለቲካ ቁማር በዓለም በተለያዩ ሀገራት (ሩስያ፣ ቻይና…) ታይቷል። ሕገወጡ ሕወሃትን ጨምሮ በዓለም ላይ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ወገኖች ሥልጣን ለመያዝ ሲሉ የጋራ ግንባር ይፈጥራሉ። ነገር ግን ሥልጣን ላይ ሲወጡ ያሻገራቸውን አጋር ኀይል ጠራርገው ያጠፋሉ።
የፖለቲካ ተንታኞች ይህንን አካሄድ የጊንጥ ፖለቲካ በማለት ይገልጹታል። ጊንጡ ወንዝ እስኪሻገር አዝሎት የነበረውን እንስሳ ከተሻገረ በኋላ መውጋቱ አይቀርምና።
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክም ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የፖለቲካ አካሄድ የዚሁ ባህሪ ዋነኛ ማሳያ ነው። ቡድኑ ከበረሃ ትግሉ ጀምሮ እስከ ሥልጣን ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ ይህንኑ ስልት ተጠቅሟል።
የፖለቲካ አጥኝዎች እና የቀድሞ አጋሮቹ በተደጋጋሚ እንደመሰከሩት ቡድኑ ሥልጣን እና ጥቅምን ከሌሎች ጋር እኩል የመካፈል ባሕልም ኾነ ፍላጎት የለውም። ኢሕአዴግን ሲመሰርትም ኾነ ሌሎች አጋር ድርጅቶችን ሲፈጥር አላማው የራሱን የበላይነት ማረጋገጥ ብቻ ነበር። አጋሮቹን የተጠቀመባቸው እንደ ማጀቢያ እና መጠቀሚያ በማድረግ ነበር።
የፖለቲካ ተንታኞች የሕገወጡ ሕወሃትን አካሄድ ሲገመግሙ ቡድኑ ሁልጊዜም “የጠላቴ ጠላት ለእኔ ወዳጄ ነው” በሚል ጊዜያዊ ጥምረቶችን እንደሚፈጥር ይገልጻሉ። አቅም ሲያገኝ ወይም አካሄዱ እንደማያምር ስጋት ሲገባው ግን ትላንት የረዱትን ኀይሎች እንደ ስጋት ይመለከታቸዋል። እርስ በእርስ ያጋጫል፤ በውስጣቸው ሰርጎ በመግባት ያከፋፍላል፤ ያዳክማል።
የቡድኑ የፖለቲካ መሠረት ጽንፈኛ፣ አግላይ እና ራስ ወዳድ በመኾኑ እውነተኛ እና ዘላቂ አጋርነትን አይቀበልም። መርህን መሠረት ያላደረገ ጥምረት በመፍጠር ሌሎችን ማስበላት ታሪካዊ ልማዱ ኾኗል።
በአሁኑ ወቅትም የተወሰኑ ኀይሎች ይህንን የታሪክ ትምህርት ዘንግተው የቡድኑ ሰለባ እየኾኑ ነው። ብሶታችንን ይፈታል በሚል ስሌት ተሰልፈው አጀብ እያሉት ነው። ቡድኑ ግን የነሱን ብሶት የሚጠቀመው ጊዜያዊ አቅም ለማግኘት ብቻ ነው። የራሱን ጠባብ ፍላጎት ካሳካ አለያም አሸናፊነት እንደማይቀናው ካወቀ እነዚህን ኀይሎች አደጋ ላይ መጣሉ አይቀርም።
የዓለም ሀገራት ተሞክሮም ኾነ የሕገወጡ ሕወሃት ተግባራዊ ታሪክ የሚያረጋግጠው የሌሎችን ብሶት በማራገብ ብቻ የሚመሰረት ጥምረት መጨረሻው አጃቢዎችን ማስበላት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ኢትዮጵያ በእናቶች እና በሕጻናት ሞት ቅነሳ ላይ ለውጦችን አስመዝግባለች” ዶክተር መቅደስ ዳባ