
የዘመን መለወጫን መቃረብ ተከትሎ የክረምቱ ደመና ገፈፍ ብሎ ምድር በአደይ አበባ ስትፈካ፣ በአማራ ክልል የሚከበሩት ተከታታይ በዓላት የባሕል እና የማንነት ሕያው ሥዕሎች ኾነው ይቆማሉ። እነዚህ በዓላት ከግለሰብ አልፈው የጋራ ሥነ-ልቦናን የሚገነቡ፣ ማኅበራዊ ትስስርን የሚጠብቁ እና አብሮነትን የሚያረሰርሱ የማይታዩ የማንነት ዐምዶች ናቸው።
በዋናነት የልጃገረዶች መብት፣ ነፃነት እና ውበት በደማቅ ዜማ እና ጭፈራ የሚገለጽባቸው ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል የብሩህ ዘመን መባቻዎች ናቸው። ወጣት ሴቶች በባሕላዊ አልባሳት አሸብርቀው እና ጌጣጌጥ አድርገው በእኩልነት እና በእህትማማችነት ስሜት በጋራ ሲዘምሩ የትውልድ ክፍተትን ከመድፈኑም ባሻገር በኅብረተሰቡ ውስጥ የሴቶችን ክብር እና ቦታ በጉልህ ያሳያል።
“ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት የበዓላት ቱሪዝምን የማሥተዳደር ተግዳሮቶች እና መልካም አጋጣሚዎች” በሚል በክልሉ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው እነዚህ በዓላት የማኅበረሰቡን የማይዳሰሱ እሴቶች፣ ታሪክን፣ ቋንቋን፣ እና ስለ ተፈጥሮ ያለን ዕውቀት አቅፈው የያዙ ብርቱ የቱሪዝም መሠረቶች ናቸው።
ልጃገረዶቹ ሻደይን እና አሸንድዬን አክብረው ሲመለሱ፣ የክረምቱን ማብቃት እና የአዲሱን ዓመት ንጽህና አዝለው የሚገቡት እንግጫ እየነቀሉ እና ከሴ እያጨዱ ነው። ይህ ክዋኔ ሰው ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ስምምነት ከማሳየቱም በላይ አዲሱን ዓመት በይቅርታ ለመቀበል የሚደረግ ማኅበራዊ የጽዳት ሥነ-ሥርዓት ነው።
በዓላቱ በዜማዎቻቸው በሚያስተላልፉት የፍቅር መልዕክት በሰዎች መካከል ያለውን ቂም እና ቁርሾ አጥበው በማስወገድ በተጣሉ ቤተሰቦች እና ጎረቤቶች መካከል እርቅን ያወርዳሉ።
የብርሃን እና የድል ተምሳሌት የኾኑት መንፈሳዊ በዓላት ደግሞ የዚህ ሁሉ የባሕል ዐውደ ርዕይ ማሳረጊያ ይኾናሉ። በመስቀል ደመራ እሳት ብርሃን ዙሪያ የሚሠበሠበው ሕዝብ የሀብት፣ የዕድሜ ወይም የሥልጣን ልዩነት ሳያግደው እኩል ሲቆም ሰው ሠራሽ ማኅበራዊ መደቦችን አፍርሶ የእኩልነትን ትርጉም በተግባር ይሰብካል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማኞችን አንድ አድርጎ የሚያስተሳስረው ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ የሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ሰዎች በመንገድ ላይ የሚረዳዱበት፣ እንጀራቸውን እና ውኃቸውን የሚካፈሉበት፣ የጋራ መከራን እና ደስታን የሚጋሩበት ፍጹም የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት ነው።
ከተፈጥሮ ዑደት ጋር ተቆራኝተው ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበሩት በዓላት ተራ መዝናኛዎች ብቻ አይደሉም። የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክሩ፣ ሰላምን የሚያሰፍኑ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍቅርን፣ ይቅርታን እና አብሮነትን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ የማይተኩ የማኅበራዊ ፈውስ እና የግንባታ መሣሪያዎች ጭምር እንጂ።
የንፁህ ኢትዮጵያዊ ማንነት መታወቂያ የኾኑትን እነዚህን በዓላት ለማክበር ዝግጅት መደረጉንም የክልሉ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያሳያል።
#አሚኮ #ባሕል_ማንነት_አንድነት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_16_2018_ዓ_ም
✍️ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
