
“ወደ ጫካ የወጣነው ምክክር ባለመኖሩ ነው” ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ
በመርጦ ለማርያም ከተማ ነው የተወለዱት። በወጣትነት ዘመናቸው ለሀገራቸው በሀገር መከላከያ ሠራዊት በአየር ኀይል ካፒቴንነት አገልግለዋል። በሕገወጡ የሕወሃት ቡድን የሥልጣን ዘመን በእስር ላይ አሳልፈዋል።
በለውጡ ወቅትም ከእስር ነጻ ኾነዋል። በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት የታጣቂ ኀይሎችን ሲመሩም ቆይተዋል። የግጭትን አክሳሪነት እና በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመገንዘባቸው ከጓደኞቻቸው ጋር የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል። በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ምክክር ለአንዲት ሀገር አስፈላጊ መኾኑን ይገልጻሉ። ምክክሩ በ1960ዎቹ አካባቢ ተካሂዶ ቢኾን መንግሥታት ሲቀያየሩ የሚፈጠረውን እልቂት ማስቆም፤ የምሁራንን እና የዜጎችን ሕይወት ማዳን ይቻል እንደነበር ይናገራሉ።
የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት አካታች፤ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
“ወደ ጫካ የወጣነው ምክክር ባለመኖሩ ነው” ያሉት ካፒቴን ማስረሻ የእኔ ቁስል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቁስል ነው ብሎ መነጋገር ባለመቻሉ የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው እንደነበር ያነሳሉ። በትጥቅ ትግል የሕዝብን መከራ ማራዘም ብቻ እንጅ ጥቅም የለውም የሚል አቋም አላቸው።

ፍላጎታቸው መነጋገር ብቻ ስለነበር ከመንግሥት ጋር ድርድር በማድረግ የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን ገልጸዋል። አሁንም የሀገራቸውን እጣ ፈንታ ለመወሰን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ እየተሳተፉ መኾኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እንድንከፋፈል አድርገውናል ነው ያሉት። በግጭት፤ በጦርነት ያመጣነው ለውጥ የለም ይልቁንም በግጭት ትውልድ እየገደልን፤ ሕዝብ እያሰቃየን፤ የሀገርን ዕድገት ወደ ኋላ እየመለስን ነው ብለዋል።
አንዱን ጨቋኝ አንዱን ተጨቋኝ፤ አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ደግሞ ተጎጅ በማድረግ ሀገር ልናራምድ አንችልም ብለዋል። የውጭ ኀይሎች በስሜት የሚነዳ ትውልድ እንዲፈጠር እየሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል። ለሀገር በማሰብ ውይይትን በማስቀደም የጠላቶችን ሤራ ማክሸፍ ይገባልም ነው ያሉት።
ታጣቂዎች በሕዝብ ጥያቄ ስም የራሳቸውን ጥቅም እንደሚያፈሩ ተናግረዋል። ሀገር የምትመሠረተው በምክክር መኾኑንም ገልጸዋል።
ሕዝብ ያለ ልዩነት በመምከሩ፤ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች በሃሳብ የበላይነት እና በመነጋገር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በምክክሩ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳሳደረባቸው አንስተዋል።
#አሚኮ #ሀገራዊምክክር#ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
