
የሕገ ወጡ ሕወሃት ነገር – ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ
ተፈጥሮአዊ ወይም አብሮ ያደገ መጥፎ ባህሪ በእድሜ መግፋት፤ በምክር እና በተግሳጽ እንደማይለቅ ይልቁንም አብሮ እንደሚዘልቅ እና ተደጋግሞ እንደሚገለጥ ለማሳየት “ጅል አመል አይለቅም” ይላሉ ኢትዮጵያውያን በብሂላቸው።
አባባሉ ሕገ ወጡን ሕወሃት በአግባቡ ይገልጸዋል። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥርዓት በቅርበት የሚያውቁ ሁሉ ሕገ ወጡን ሕወሃትን ሲገልጹት ቢመከር የማይሰማ፤ ጊዜ እና ዘመን የማይቀይረው፤ መከራ እንኳን የማይመክረው፤ በሴራ እና በተንኮል ጫካ ተወልዶ፤ በጥፋት ጫካ ውስጥ ሊቀበር እየተንደፋደፈ የሚገኝ እኩይ ቡድን ነው ይሉታል።
ለ27 ዓመታት በስመ መንግሥትነት ሀገር እና ሕዝብን የዘረፈው ይህ ሕገ ወጥ ቡድን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የዘረጋው አምባገነናዊ መዋቅር በሕዝብ እና በውስጣዊ አመራር የተቀናጀ ትግል ከተወገደ እነኾ አስር ዓመታት ሊደፍን ተቃርቧል።
ይሁን እንጅ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የመቀበል ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌለው ሕገ ወጥ ቡድኑ አሁንም ወደ ሥልጣን የመጣበትን መንገድ እንደመረጠ ነው። አሁንም የትጥቅ ትግልን አማራጭ በማድረግ ጫካ ገብቶ ሕዝብን እና ሀገርን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
ገና ከጫካ ሕይወቱ ጀምሮ እስከ አሁን ሀገር እና ሕዝብን መዝረፍ፤ ጦርነት፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት፤ የሐሰት ትርክቶችን እና ፕሮፖጋንዳዎችን መፍጠር፣ መረጃዎችን ማዛባት እና ሁልጊዜም ቢኾን ራሱን ተበዳይ አድርጎ ማቅረብ የሕገ ወጡ ሕወሃት ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው።
ከሰሜኑ ጦርነት መነሻ ጀምሮ እስከ ሰሞኑ አጥፊ ትንኮሳዎቹ ድረስ ራሱ ትንኮሳ ፈጻሚ ኾኖ ሳለ ጥቃት ተፈጸመብኝ ባይ አሳሳች የፕሮፓጋንዳ ስልቱ የቡድኑን ተፈጥሯዊ ስሪት ግልጥልጥ አድርገው የሚያሳዩ ክስተቶች ናቸው።
በ2013 ዓ.ም በጥንቃቄ አቅዶ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ታሪካዊ ክህደት እና ጥቃት ሲፈጽም የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ ለማስከበር የወሰደበትን እርምጃ “የህልውና አደጋ ተጋረጠብኝ” በማለት የትግራይ ክልል ሕዝብን ለጦርነት ማገዶነት ያሰለፈበት አግባብ የቡድኑን አሳሳች ፕሮፖጋንዳ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶ አልፏል። ሕዝብ ዋጋ ቢከፍልም ብዙ ተምሮበታል።
የትግራይ ክልል ሕዝብ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፣ ልማትን እና መረጋጋትን ቢመኝም ሕገ ወጡ ሕወሃት ግን የክልሉን ሕዝብ “የውጭ ጠላት ተደቅኖብሃል” በሚል ፍርሃት ሸብቦ ራሱን ከተጠያቂነት ማምለጫ አድርጎም ይጠቀምበታል።
“ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ የሕገ ወጥ ቡድኑ የተለመደ ባህሪ አሁንም አለቀቀውም። ከሰሞኑ ከተለያዩ የውጭ ጠላቶች እና ከውስጥ ሕገ ወጥ ታጣቂዎች ጋር በመቀናጀት ጦርነት እንደሚከፍት ሲዝት የሰነበተው ሕገ ወጡ ሕወሃት በተለያየ አካባቢ ለፈጸመው ትንኮሳ በመንግሥት አጸፋ ምላሽ ሲሰጠው ” ትንኮሳ ተፈጸመብኝ” በማለት የተለመደ ጩኸቱን ሲያሰማ ሰንብቷል።
“ጦርነት እንከፍታለን፥ መንግሥትን በኃይል እናስወግዳለን” ብሎ እየዛተ የሚገኝ አካል “ትንኮሳ ተፈጸመብኝ” ብሎ መጮኹ ምን የሚሉት አመል ነው? ጅራፍ ራሱን ገርፎ ራሱ እንደሚጮኸው።
ጦርነትን ከሩቅ እየሸሸ፤ ሰላምን አጥብቆ እየሻተ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብም ለሕገ ወጡ ቡድን ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሰላሙን ለመጠበቅ ዝግጁ ነው። እንደ ቀድሞው በሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚሸወድ የትግራይ ሕዝብም እንደሌለ በገሃድ እየታየ ነው። ታዲያ ለሰላም መሥራት እዚህ ላይ ተገልጧል። አጥፊዎችን አለመተባበር፤ ወግድ አንተ አትጠቅመኝም ማለት። እንዲህ ሲኾን አጥፊዎች መደበቂ ያጣሉ፤ የሚፈለገው ሰላምም ይመጣል።
አንድ ሉዓላዊ ሀገር የራሷ የኾነ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲኖራት የሚደረገው በዋነኝነት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ የሀገርን ዳር ድንበር ለመጠበቅ እና የዜጎችን ደኅንነት ከሀገር ውስጥም ኾነ ከውጭ ከሚሰነዘሩ ጥቃቶች ለመከላከል መኾኑ ለማንም ግልጽ ነው። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግሥት በሕገ ወጥ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ መብቱ እና ኀላፊነቱ በሕገ-መንግሥቱ እና በዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ በግልጽ የተቀመጠ መኾኑም ሊረሳ አይገባውም።
እንደ ሕወሃት ያለ ሕገ ወጥ እና አጥፊ ቡድን ደግሞ እንደ ስለት ልጅ እንደፈለክ ሁን አይባልም። አስፈላጊ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ እንደኾነ ለሀገሪቱ ሰላም የሚመኙ ሁሉ የሚሰጡት ሀሳብ ነው።
#Ameco #NoMoreWar #PeaceForEthiopia
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
