በውበት ላይ ውበት የደረበችው ባሕርዳር።

7
ዘመናትን በተፈጥሮ እቅፍ ውስጥ ተሸሽጋ በጣና ሐይቅ ሰማያዊ ማዕበል ወዝ እየረሰረሰች በዓባይ ወንዝ ታላቅነት ታጅባ የኖረች የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ዕንቁ ናት ባሕርዳር።
ባሕር ዳር የሚከትም እንግዳ ገና ከሩቁ የሚቀበለው የአየር ፀባይ፣ በየመንገዱ ዳር የተተከሉት የዘንባባ ዛፎች ወለል ብለው የሚሰጡት ሰላም እና በነዋሪዋ ፈገግታ የታጀበ ረጋ ያለው መስተንግዶ ከተማዋን የተለየ የህሊና ማረፊያ ያደርጋታል። የጣና ሐይቅ አየርን ኮሪደር ልማቱ በገለጠው የመተንፈሻ ቱቦ እየሳበች በሞቃታማ አየር የታፈነውን ሳንባዋን አድሳለች።
የጥንታውያኑ ገዳማት እና የደሴቶቿ ምስጢር ተደምሮባት ከተፈጥሮ ስጦታ በላይ የመንፈስ ማደሻ ስፍራ መስላ እንድትኖር አድርጓታል። የዓባይ ፏፏቴ የሚያወጣው የውኃ ብናኝ እና የሚፈጥረው የቀስተደመና ውበት ደግሞ ለዚች ከተማ ዘላቂ አክሊል ኾኖላታል።
ለዘመናት በተፈጥሮ ጸጋዋ ብቻ ተከብራ የኖረችው ይህች ውብ ከተማ ዛሬ ደግሞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ቆማለች። የኮሪደር ልማቱ ሲታከልባት ውበቷ ከቀደመው ይበልጥ ደመቀ። የተፈጥሮ ስጦታዋ ከዘመናዊ የመሠረተ ልማት ዕይታ ጋር ተዋሕዶ የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀየረው። በውበት ላይ ውበት አጎናጸፋት።
የኮሪደር ልማቱ በጥላማ ዛፎች የታጠሩትን አደባባዮች እንዲታደሱ ምክንያት ኾናት። መለያዋ የኾነውን የብስክሌት ግልቢያ ዳግም ሊያነግስ ከእግረኛ መንገዶች እኩል የብስክሌት መንገድ ፈጠረላት። የውኃ መዋኛ ነባር ገንዳዎቿም ታደሱላት። ኮሪደር ልማት ከነበራት ጸጋ ላይ ለከተማዋ አዲስ ሕይወት ዘርቶላታል።
ፀሐይ በጣና ሐይቅ ጓሮ በኩል ስትጠልቅ የኮሪደሩ የውበት መብራቶች በየመንገዱ በርተው ባሕርዳርን በሌሊትም የምታበራ የወርቅ ምድር አስመስለዋታል። የሐይቁን ዳርቻ ሳይበክሉ የዘንባባዎቹን ውበት ሳይጋርዱ የተዘረጉት ዘመናዊ መናፈሻዎች እና የእግር መንገድ መስመሮች ከተማዋን ለነዋሪዎቿም ኾነ ለእንግዶቿ ተመራጭ መዝናኛ አድርገዋታል።
ባሕርዳር አሁን የትላንትና ተፈጥሯዊ ድምቀቷን ከዛሬው ዘመናዊ የኮሪደር ልማት ጋር አጋብታ የቀጣይ ዘመን የአፍሪካ የቱሪዝም እና የውበት ማዕከልነቷን በኩራት እያወጀች ትገኛለች። ጣና ሲወዛወዝ፣ ዓባይ ሲገሰግስ፣ የኮሪደሩ መንገድ ደግሞ ፈገግ ብሎ እንግዳውን ሲቀበል ባሕርዳር ዘላቂ የውበት ተስፋ መኾኗን ይመሰክራል።
✍️በሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናልን መረቁ ።
Next article“መንግሥት ሌብነትን እና ሕገወጥነትን ለመከላከል ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት