“ትልቁ ጉባኤ ሊጀመር አፋፍ ላይ እንገኛለን ” ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

23
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የዕለቱን ውሎ እና ቀጣይ ሂደቶች በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ የምክክር ጉባኤው ሰሞኑን ስልታዊ ቡድን ላይ (50ዎቹ 80 ቦታ )ተከፋፍለው ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ሀምሳዎቹ ለራሳቸው ወይም ስልታዊ ለሚባለው 250 ኾነው እና 16 ቦታ ላይ ለተከፋፈሉት የራሳቸውን አጀንዳ በሚገባ እያቀረቡ የጎደለውን እየሞሉ፤ ሊያቀራርቧቸው የሚገቡ ሀሳቦችን እያካተቱ ብዙ ውይይት በማድረግ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲመካከሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
አሁን የ 250ዎቹ የተጠናቀረ አጀንዳ ለዋናው 500 ቡድን የሚቀርብ መኾኑን አሳውቀዋል።
ከየክልሉ የመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወጣቶች፣ ሲቪክ ማኅበራት እና ሌሎች ወኪሎቻቸው በተሰጣቸው ኮታ መሠረት በክልል እና በፌዴራል ተቋማት ደረጃ ቡድን እንዲመርጡ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህ አሠራር መሠረት ወደ 330 የሚኾኑ ተወካዮች ቡድኑን እንዲመርጡ ተደርገዋል ነው ያሉት። 12 ክልሎች፣ ሁለት ከተማ መሥተዳድሮች እና የፌዴራል ተቋማት 15 ቦታ ተከፋፍለው ተወካዮችን እንዲመርጡ ተደርጓል ብለዋል።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ በ 250ዎቹ ተመካካሪዎች የቀረቡላቸውን ሰነዶች ተመካካሪዎቹ ራሳቸው ያነሷቸው ጉዳዮች መኾናቸውን በሚገባ አረጋግጠው የመፈራረም ሥራ ያከናውናሉ ብለዋል። ይህም በሚቀጥለው ሰኞ ወደሚካሄደው ትልቁ ጉባኤ ይወስዳቸዋል ነው ያሉት።
ሰኞ የሚካሄደው ዋና ጉባኤ ስምንት ቦታ የሚካሄድ ኾኖ እያንዳንዱ በቁጥር 500 ተመካካሪዎች የሚሳተፉበት መኾኑንም ገልጸዋል። እነዚህም በሚቀጥሉት ሳምንታት በተነሱ ጉዳዮች ላይ ወደበለጠ መግባባት በሚወስዷቸው አግባቦች በሚገባ ይመካከራሉ ብለዋል።
በሚቀጥለው ሰኞ ተመካካሪዎች ችግኝ በመትከል ወደምክክራቸው እንደሚገቡ ዋና ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።
ትልቁ ጉባኤ ሊጀመር አፋፍ ላይ እንገኛለን ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ትልቁ ጉባኤ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል ብለዋል። ሥራዎቹን ሲጀምር ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደ አስፈላጊነቱ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የዕውቀት ግብዓት ይሰጣሉ ነው ያሉት። ግብዓት የሚሰጠው በተመካካሪዎች ፍላጎት እና ጥያቄ መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመግባባት የተደረሰባቸው አጀንዳዎች በቀጣይ 500 አባላት ላሉት ጉባኤ ይቀርባሉ።
Next articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ከጎንደር ሁመራ ቋሚ የበረራ አገልግሎት ሊጀምር ነው።