እብሪትና የደም ጥማት – የሕገ ወጡ ሕወሃት የጦረኝነት አባዜ ⚔️

3

 

የሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የፖለቲካ ትርክት ገና ከፅንሰቱ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን እንደ የጋራ ማንነት ከመቀበል ይልቅ በጠላትነት በመፈረጅ ላይ የተመሰረተ ነው። ቡድኑ በማኒፌስቶው ሳይቀር ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንደ ጨቋኝ በመፈረጅና የትግራይን ህዝብ ከሌላው ወንድሙ በማጋጨት ኢትዮጵያ ጠል የኾነ ርዕዮተ ዓለምን በይፋ ተክሏል።

የተቀናሽ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ማኅበር ፕሬዚዳንት አስር አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ነው፤ ቡድኑ በጥላቻ የሰከረ፣ ጸረ-ኢትዮጵያዊ አቋም ያለውና “እኔ ከሌለሁ ሌላው መኖር የለበትም” በሚል የእብሪትና የብቸኝነት ስሜት የሚመራ ነው። ቡድኑ ስልጣን ከያዘ በኋላም ቢኾን ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲጠራጠሩና እንዲቃቃሩ በማድረግ የሀገር ውስጥ አንድነትን ኾን ብሎ ሲያላላ ቆይቷል።

ይህንን የተንጋደደ ህልውናውን ለማስቀጠል የተጠቀመበት ዋነኛው ስልት ደግሞ የትግራይን ህዝብ በከበባ ስነ-ልቦና ውስጥ ማቆየት ነበር። ቡድኑ የትግራይ ህዝብን “የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ሊያጠፋህ ነው፤ ብቸኛው መከታህ እኔ ነኝ” በሚል የፍርሃት ፖለቲካ ውስጥ ዘፍቆት ቆይቷል፣ ይህንን ያረጀ ያፈጀ ስልታቸው ዛሬም ድረስ በኩራት ሲናገሩት ይደመጣል። ይህ አካሄድ የትግራይን ወጣት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር እንዳይግባባና በጥርጣሬ እንዲተያይ ትልቅ ግድግዳ የገነባ የፖለቲካ ሴራ ሲኾን፣ በተለይም ከ2010 ዓ.ም የፖለቲካ ለውጥ በኋላ ወደ መቀሌ በማፈግፈግ ስልታዊ የኾነ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል።

የዚህ እኩይ ፕሮፓጋንዳና የጦረኝነት ባህሪ እንዲሁም የሀገር ክህደት ተግባር ቁንጮ ኾኖ የሚመዘገበው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ለበርካታ ዓመታት የትግራይን ህዝብ ከባዕድ ጠላት ሲጠብቅ፣ አብሮ ሲበላና በሕዝብ የልማት ሥራዎች ላይ ሲሳተፍ ኖሯል። ቡድኑ ግን ይህንን የህዝብና የሠራዊት ትስስር ወደ ጎን በመተው በጨለማ ጀርባን የማጥቃት እርምጃ ወስዷል።

ቡድኑ የፈጸመው ይህ ጥቃት ተራ ወታደራዊ ግጭት ሳይኾን የሀገርን ሉዓላዊነትና የደህንነት ምሰሶ በማፍረስ ኢትዮጵያን ወደማያባራ የእርስ በርስ ጦርነትና የመበታተን አደጋ ውስጥ ለመክተት የተደረገ አረመኔያዊ የክህደት ተግባር ነበር፤ ቡድኑ እርምጃውን ‘መብረቃዊ ጥቃት’ ብሎ ማመኑም የጦረኝነት ባህሪውን በግልጽ ያሳያል።

የዚህ የህገወጡ ቡድን እብሪትና ጦረኝነት ከማንም በላይ ከባድና መራር ዋጋ ያስከፈለው የትግራይን ሕዝብ ነው። አስር አለቃ ደጀኔ እንደሚናገሩት ለቡድኑ የሥልጣን ጥማት ሲባል ብቻ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ የማያባራ የጦረኝነት አባዜ ሦስት ተከታታይ ትውልዶችን በከንቱ የጦርነት እሳት ማግዶ አስገብሯል።

ቡድኑ ከበረሃው የትጥቅ ትግል ዘመን አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜው የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ድረስ የትግራይ ወጣት ለድርጅቱ የፖለቲካ ቁማር ማካሄጃና የጥይት ማብረጃ ኾኖ ቆይቷል። በዚህም የትግራይ ክልል ኢኮኖሚ፣ የጤና ተቋማትና መሰረተ ልማቶች ወደ ኋላ እንዲመለሱ አድርጓል፤ ህዝቡም በጦርነቱ ምክንያት ለከፋ ረሃብ፣ መፈናቀልና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ተዳርጓል።

ይህንን ሀቅ በማጠናከር አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) እንደሚገልጹት የሕገ ወጡ ቡድን አመራሮች ለትግራይ ህዝብ የማይጨበጥ ተስፋ በመስጠትና ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት በተለይም የወጣቱን አዕምሮ በመመረዝ በሰሜኑ ጦርነት በከንቱ እንዲያልቅ አድርገዋል። ቡድኑ አሁንም ለህዝብ የቆመ በማስመሰል የውሸት ትርክት ቢያራምድም እውነተኛ ዓላማው የህዝቡን ስቃይ ማቅለል ሳይኾን የራሱን ጠባብ የፖለቲካ ጥቅም ማስጠበቅና ስልጣኑን ማራዘም ብቻ ነው ብለዋል። ይህ የጥፋት ሴራቸው እንዳይጋለጥ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ማንም እንዳይናገር፣ እንዳይጽፍ፣ እንዳይደራጅና የተለየ ሐሳብ እንዳያራምድ ፍጹም አፈና እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ይባስ ብሎ የቡድኑ የጦረኝነትና የጥፋት ባህሪ ትላንት በታሪክ ማህደር የተዘጋ ሳይኾን ዛሬም ድረስ የቀጠለ ነው። ቡድኑ ካለፈው ጥፋቱ ተምሮ ለህዝቡ እፎይታን ከመስጠት ይልቅ ዛሬም ኢትዮጵያ ጠል ከኾኑ የባዕዳን ኅይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር “ዳግም ኢትዮጵያን ለመውጋት ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ” እያለ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል። ይህ ድርጊቱ የሚያሳየው የቡድኑ አመራሮች ለትግራይ ህዝብ ህይወትና ደኅንነት ቅንጣት ታክል ደንታ የሌላቸው፣ ጠባብ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ብቻ ሀገርን ከማፍረስና ከውጭ ጠላቶች ጋር አብሮ ከመስራት ወደኋላ የማይሉ መኾናቸውን ነው።

በአጠቃላይ ከ1968ቱ ማኒፌስቶ እስከ ሰሜን ዕዝ ክህደትና የአሁኑ የጦርነት ዝግጅት የሚያረጋግጠው ህገወጡ ሕወሓት ስልጣኑን ለማቆየት ሲል የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚያጋጭና ማንኛውንም የጥፋት እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ የማይል መኾኑን ነው። ይህ የጥፋት ዑደት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን የትግራይ ህዝብን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ የቡድኑን እኩይ ሴራ በጋራ ሊያወግዘውና በጽናት ሊታገሉት ይገባል።

#ጦርነት_በቃ #ሰላም_ለኢትዮጵያ #ኢትዮጵያ #የሕወሃት_ሴራ #የሀገር_አንድነት #የሀገር_ሰላም #Ethiopia #PeaceForEthiopia #NoMoreWar

ስማቸው አጥናፍ

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🛑እድሜ ልኩን የስልጣን ፍላጎትን በሕዝብ ደም የሚመኘው ሕገ ወጡ ሕወሃት።
Next article“እድሜ ልክ – ከሰላም የራቁ”