🛑 የወጭት ሰባሪው የፖለቲካ ቅዤት እና የ”እዘሉኝ” ጥሪ!

5

 

ሀገርን እናልማ ሲባሉ በተቃርኖ ቆመው የሚቀሩ፤ ሀገር እና ሕዝብ ታግሷቸው እንኳን ግፍና በደላቸው ከትዕግስትም በላይ ሞልቶ የሚፈስስ የሀገር ልጆች፣ ግን ደግሞ የሀገር ደመኞች ምንጊዜም ቢኾን አሉ። እነዚህ አካላት በአካልም በአምሳልም ኢትዮጵያዊ ኾነው፣ ግብራቸው ግን ከሀገር ወጥቶ የኮበለለ “የእንግዴ ልጆች” ከመባል የዘለለ ስምም ታሪክም አይኖራቸውም። እነዚህ የእንግዴ ልጆችም ኢትዮጵያን ጀርባዋን ለማጉበጥ ከንቱ ሲቃዡ ይስተዋላሉ። አብሮ ለማልማት በተጠሩ ጊዜ ሽኩቻን ይመርጣሉ፤ ሀገር እና ሕዝብን ማተራመስ ሲፈልጉ ደግሞ ከወዲያና ወዲህ በግብር ከሚመስላቸው ጋር ተጠራርተው “ተጣመርን” ይላሉ። ምንም ቢጣመሩ የመጠላላት ግብር እንጅ ሀገር የማልማት የጋራ ርዕይ ግን ፈጽሞ የላቸውም።

በጥላቻ ውስጥ ከሚማቅቁት የህገወጡ ሕወሃት ርዝሯዦች መካከል የኾነችው ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር ከሰሞኑ በትግርኛ ቋንቋ ባስተላለፈችው መልእክት ከአማራ ክልል ጀምሮ እስከ መላ ሀገር የሚዘልቅ ጥላቻዋን አንጸባርቃለች። የአማራ ሕዝብን ታሪካዊ ርስቶች እንደገና በኃይል ለመንጠቅ ወደብጥብጥ እንደሚገቡም አመላክታች።

አስገራሚው እና ትዕቢት ንቀትን እንደሚወልድ የሚያመላክተው ግን “አማራ ክልልን ለመውረር ከአማራ ክልል ታጣቂዎች ጋር ጥምረት እንፈጥራለን” የሚለው ንግግሯ ነው። ይሄው የትብብር መልእክቷ ገና በአራት ነጥብ ሳይቋጭ እዚያው ላይ ጸረ አማራ ትርክቷን ዘክዝካለች።

የህገወጡ ሕዎሃት ርዝራዦች መነሻ መሰረታቸው በአማራ ሕዝብ ብሎም በኢትዮጵያ ጥላቻ ላይ የተመሠረተ መኾኑ ታውቆ ያደረ እና በየቀኑ ከተግባራቸውም ከንግግራቸውም የሚዘከዘክ ሀቅ ነው። ይች ሰው ባስተላለፈችው የሰሞኑ ንግግርም የአማራ ክልል ታጣቂዎችን ለጊዜያዊ ጥቅም ማሳለጫነት እንደሚጠቀሙ እንጅ ምንም አይነት የጋራ ራዕይ እንደሌላቸው አስረግጣ ገልጻለች። “እንኳንስ ከነሱ ከኢህአዴግም ተለያይተናል” በማለት አብሮ ሩቅ የሚጓዝ ዓላማ እንደሌላቸው እና ታውቆ ያደረውን “ዶሮ ሳይጮህ ሶስቴ የመክዳት” ሀቃቸውን በገዛ አፏም አፍስሳዋለች።

የዚህ ቡድን ባሕሪው “ወጭት ሰባሪነት” ታሪኩም ታዝሎ አንዳች ቦታ መድረስ፤ ከዚያም አዛዩን ገፍትሮ ገደል መክተትና ማጥፋት ነው። “አዲስ አበባ ይዘንህ ልንገባ ነው” እያሉ የደለሉት የትግራይ ወጣት የጃጀ አካላቸውን እና ጥላቻ ያደራበት ስብእናቸውን አዝሎ በየጫካው ተንከራትቷል፤ በጦርነት ማግደውት ሕልሙ በአጭር የቀረውም ቤት ይቁጠረው። የነዚህ የትግራይ ወጣቶች ደም ሳይደርቅ የአማራ ክልል ወጣቶችንም ለቀጣይ ጥፋታቸው ሰለባነት ማጨት አንድም ንቀት፤ ሁለትም “ልሞክር እስኪ” አይነት ከንቱ ምኞት ነው።

በጥላቻ ትርክት እና በሥልጣን ጥም አብዶ አዘሉና አራት ኪሎ ጣሉኝ፤ ከዚያም የለመደብኝን ሀገር የመሸንሸን አባዜ ላራምድ፤ የሰው ርስትም ልውረር ማለት ፖለቲካዊ ቅዤት ነው።

የህገወጡ ሕወሃት ርዝራዦች የ”እዘሉኝ” አካሄድ ከአዛዮቹ ጋር የርዕዮተ ዓለም መመሳሰልን የሚያሳይ ሳይሆን፣ የጋራ ኪሳራን መሰረት ያደረገ የስልጣን ጥማት እንጂ ሌላ አይደለም። ሕገ ወጡ ህወሃት የአማራን ታጣቂዎች ሀሳብ፣ ፖለቲካዊ አቋም ወይም የሚያልሙትን ጥቅም ሊያከብር አይችልም። ይልቁንም ታጣቂዎቹን እንደ መሣሪያ እና እንደ መተላለፊያ ድልድይ በመጠቀም የራሱን የጠፋ ፖለቲካ ነፍስ ለመዝራት ብቻ እየጣረ ይገኛል።

ወጭት ሰባሪን ማን ያዝል ይኾን?

በርካታ ሰላም ወዳድ የትግራይ ወጣቶች “እምቢ ለዳግም ጦርነት” ብለው እየሸሹ ነው። በፊሽካ ተጠራርተው ከዚህ ቡድን አፈና በማምለጥ ከሀገር ጎን ቆመዋል።

እንደሁለተኛ አማራጭ የታጩት ደግሞ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ናቸው። ቡድኑ በአማራ ክልል ላይ ያደረሰውን በደል የሚረሳ አለ ባይባልም ሕገ ወጡ ሕወሃት በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍ ረስቶ ይህንን ቡድን በማዘል ዳግም በሕዝብ ላይ ለማዝመት መዶለት እንኳን የአሁኑ ትውልድ መጭው ትውልድም ይቅር የማይለው ባንዳነት ነው።

​#ኢትዮጵያ #Ethiopia #የሀገርሰላም #ሕገወጡሕወሃት #የፖለቲካቅዤት #ኢትዮጵያ_ታሸንፋለች #NoMoreWar #PeaceForEthiopia

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article⚠️የሕገወጡ ሕወሃት ቡድን የዳግም እልቂት ግብዣ
Next article🛑እድሜ ልኩን የስልጣን ፍላጎትን በሕዝብ ደም የሚመኘው ሕገ ወጡ ሕወሃት።