
በአማራ ክልል በሰብል ምርት ከፍተኛ አቅም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ በኾነው በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በዚህ ዓመት ከ266 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚኾነው ማለትም ከ133 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል የተሸፈነ ሲኾን፤ ከ288 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሎ ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰውመኾን ተገኘ ገልጸዋል።
ከዚሁ የበቆሎ እርሻ ውስጥ 114 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም አሠራር የተዘራ ሲኾን የዝናብ ሁኔታው ወጥ ባይኾንም በአሁኑ ወቅት ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የዞኑ አካል በኾነችው የጃቢ ጠህናን ወረዳ በመኸር ምርት ዘመኑ በተለያዩ ሰብሎች ከሚሸፈነው 52 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 30 ሺህ ሄክታሩ በበቆሎ የተሸፈነ ነው። የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ ሞሴ እንደገለጹት ከወረዳው የበቆሎ እርሻ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል።
ለዚህም ስኬት ከ 128 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።
የወረዳው ምክትል አሥተዳዳሪ የቻለ ይርጋ በበኩላቸው አርሶ አደሩ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ተፅዕኖ ወጥቶ ግብርናውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውን ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን እና ግብዓቶች በፍትሐዊነት በመቅረባቸው ሰብሉ አሁን ላይ የተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የጃቢ ጠህናን ወረዳ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በወቅቱ በቀረበላቸው የግብዓት አቅርቦት እና በኩታ ገጠም አሠራር የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የጉልም ደንጅን ቀበሌ ነዋሪ
አርሶ አደር ሻረው ዋሌ”ሁለት ሄክታር መሬቴን በበቆሎ ሸፍኛለሁ። ባለፈው ዓመት በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት አግኝቼ ነበር፤ ዘንድሮም በቂ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ ስለቀረበልኝ የተሻለ ምርት እጠብቃለሁ” ብለዋል።
የወይንማ ወርቅማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደጉ መላክ አንተነህ “ስምንት ሄክታር መሬቴን በበቆሎ ሰብል ሸፍኛለሁ። በአካባቢያችን ሰብልን በኩታ ገጠም መዝራት የተለመደ በመኾኑ ምርታችን በየዓመቱ እየተሻሻለ መጥቷል። አሁን ላይ የተባይ እና የአረም አሰሳ በማድረግ ሰብሌን እየተንከባከብኩ በመኾኑ ከወትሮው የተለየ ምርት እጠብቃለሁ” ብለዋል
በአጠቃላይ በዞኑም ኾነ በወረዳ ደረጃ የግብዓት አቅርቦት በወቅቱ መሟላቱ እና የአርሶ አደሮች የእንክብካቤ ሥራ ተዳምሮ፣ በያዝነው የምርት ዘመን ከፍተኛ የበቆሎ ምርት እንደሚሠበሠብ ተስፋ ተጥሎበታል።
#አሚኮ_ዜና #ግብርና_ምዕራብ_ጎጃም #አማራ_ክልል
#ፍኖተ_ሰላም፡ ሐምሌ11/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ንጉስ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
