‘ሁሉም የተሳተፉበት፣ ያለ ልዩነት የተካተቱበት‌”

3

 

ሀገር የሁሉም ናት፤ ለሁሉም ታስፈልጋለች፤ ሁሉም ያስፈልጓታል፡፡ ሀገር የምትጸናው ሁሉም ልጆቿ አስተዋጽዖ ሲያደርጉባት፣ ሁሉም ልጆቿ ሲጠብቋት፣ በአንድነት ሲቆሙላት፣ በጽናት ሲያገለግሏት፣ ችግራቸውን በውይይት እየፈቱ ሰላምን ሲያጸኑላት፣ ግጭትን ሲያርቁላት እና ጦርነትን ሲያስቀሩላት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የተከበረችው በልጆቿ ብርታት፣ አንድነት እና ጽናት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት የነጻነት ብርሃን ያበራችው በልጆቿ አትንኩኝ ባይነት፣ አይደፈሬነት እና ጀግንነት ነው፡፡

በአንድነት ባይቆሙላት፣ በጀግንነት ባይጸኑላት፣ እንደ ዓለት ባይጠነክሩላት ኖሮ ኢትዮጵያ ነጻነቷን አታስጠብቅም፣ ክብሯን አታስከብርም ነበር፡፡ ለሀገር መጽናት የሁሉም ብርታት ያስፈልጋልና ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ መጽናት ያለ ስስት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ ለሀገራቸው ራሳቸውን ማስዋዕት አድርገው አቅርበዋል። በመስዋዕትነታቸውም ሀገራቸውን ጠብቀዋል፡፡ ለዘመናት የተከበረች እና የታፈረች እንድትኾን አድርገዋል፡፡

ከጥንት ጀምሮ ሀገራቸውን በደም እና በአጥንት እንደ አጸኗት ሁሉ እነኾ ዛሬ ደግሞ ሀገራቸውን በምክክር ሊያጸኗት፣ በምክክር ችግሮቿን ፈትተው ሰላም እና አንድነትን ሊያጠነክሩላት በአንድ አዳራሽ ተሠባሥበዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ቤት ናት፣ በጋራ የሚኖሩባት፣ በደስታቸው የሚደሰቱባት፣ በሀዘናቸውም በጋራ የሚያዝኑባት፡፡ ኢትዮጵያ ዓለት ላይ መሠረቷን ያጸናች፣ መሰሶዋን ያጠነከረች፣ ማገሯን ያበረታች ናት፡፡ ይህችን ሀገራቸውን የበለጠ ሊያበረቷት፣ የበለጠ ሊያጠነክሯት በጋራ ተሠባሥበዋል፡፡ ለምክክርም ተቀምጠዋል፡፡

ይህ የምክክር ጉባኤ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህ ልክ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎቻቸውን ያቀረቡበት፣ ስለሀገራቸው የመከሩበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡

ኢትዮጵያውያን እየመከሩ ነው፡፡ በምክክሩ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአንድ አዳራሽ ተገናኝተዋል፡፡ አጀንዳቸውን ይዘው ለሀገራቸው መጻዒ ዕድል ሊመካከሩ ተገናኝተዋል፡፡ የምክክር ጉባኤው ከአሁን በፊት ያልነበረ፣ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ታሪክ ያሳየ፣ ኢትዮጵያን የመሰለ፣ ኢትዮጵያውያንን የወከለ እና ያካተተ ነው።፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተመራባቸው እና ከሚመራባቸው መሠረታዊ መርሆዎች መካካል አሳታፊነት እና አካታችነት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አሳታፊ ኾኖ የማያካትት ወይም አካታች ኾኖ በሚገባው ልክ የማያሳትፍ የምክክር ሂደት ውጤታማ ስለማይኾን ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ለዚያም ነው ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ፣ ከምዕራብ ጫፍ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ኢትዮጵያውያን የተካተቱበት እና የተሳተፉበት እንዲኾን የሠራው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ያሉትን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾኑ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በሀገራቸው ጉዳይ መወሰን አለባቸው በማለት እንዲሳተፉ እና እንዲካተቱ አድርጓል፡፡
ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ በየደረጃው መሳታፍ ያለባቸው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት እንዲካተቱ እና በሚገባው ልክ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያን አለኝ የሚሉትን አጀንዳ ሁሉ አቅርበውበታል፡፡ ተሳትፈውበታል፡፡ ተካትተውበታል፡፡ ይበጀኛል በሚሉት እና በመረጡት ሰውም ተወክለውበታል፡፡

በዓለም ላይ ሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ውጤታማ ያደረጉ መሠረታዊ መርሆች አሉ፡፡ ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው፣ የመንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የታየበት፣ አካታች እና አሳታፊ የኾነ፣ ግልጽነት እና ተአማኒነት ያለው እና ገለልተኛ የኾነ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ ይኾናል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሂደትም ዓለም አቀፍ የመመዘኛ መርሆዎችን ያሟላ እና የጠበቀ ነው፡፡

እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያን መልክ እና ማንነት የመሰለ፣ ኢትዮጵያውያንንም ያሳተፈ እና የወከለ ነውና፡፡ ድሮ ፖለተከኞች ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ይወስኑላቸው እና ይወስኑባቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን አጀንዳ አቅርበዋል፡፡ ለራሳቸው ራሳቸው ሊወስኑ በአንድነት ተሠባሥበዋል፡፡

የምክክር ሂደቱ ጥቅል ዓላማው ሀገራዊ መግባባትን ማስፈን ነው፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውጤቶች ለኢትዮጵያ ችግሮች ዘላቂ የመፍትሔ ሃሳቦችን የማመንጨት ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የዚህ ዋነኛ ተጠቃሚም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ይህም ሕዝቡን የሀገራዊ ምክክሩ ግንባር ቀደም ባለቤት እንዲኾን ያደርገዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሀገር ጉዳይ ይመለከተኛል የሚልን ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን፣ ማኅበር ወይም ተቋም ድምጽ (ሃሳብ) ሰምቷል፡፡ ተቀብሏል፡፡ ይሄን ሃሳብ እና ድምጽ ይዞ ነው ለምክክር ጉባኤ የተቀመጠው፡፡ በዚህ ምክክር ያልተወከለ የኢትዮጵያ አካባቢም ኾነ ማኅበረሰብ የለም፡፡ ይህ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማንም አይደለም፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ነው፡፡ ስለ ምን ቢሉ ሁሉም የተወከሉበት እና የተሳተፉበት ነውና፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ከሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከመላው ኢትዮጵያ እና ከባሕር ማዶ ባሕር አቋርጠው የመጡ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ነው ብለዋል፡፡ በጉባኤው የተሠባሠብነው በታሪክ ምዕራፍ ላይ ሥፍራን ለሚይዝ ታላቅ ጉዳይ ነው፤ ጉባኤው የኢትዮጵያን የማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አቅጣጫ የሚያቀና፣ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ እና አስተማማኝ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ይላሉ፡፡

ምክክር ማለት ብዝኀነታችንን የምናጠፋበት ሳይኾን ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ መንገድ ይዘን በጋራ መኖር የምንችልበትን ሥርዓት የምንዘረጋበት ነው ብለዋል፡፡ የምክክር ሂደቱ አካታች እና ፍትሐዊ እንዲኾን ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎች በታማኝነት እና በገለልተኝነት ተሳትፈዋል፡፡ የሕዝቡን ዕውነተኛ ስሜት ለመለየት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎች ተሠባሥበዋል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተወክለውበታል፣ ተሳትፈውበታልና ከምክክሩ ሀገራዊ መግባባት ይጠበቃል፡፡

ሁሉም የተሳተፉበት፣ ያለ ልዩነት የተካተቱበት ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ ጉባኤ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያንን መጻዒ ዕድል የሚወስን፣ ለትውልድ መልካም ስንቅ የሚያቆይ፣ ለአፍሪካም አርዓያ እና ምሳሌ የሚኾን ነው፡፡

#አሚኮ #ሀገራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዋና ዋና ከዋኞች እነማን ናቸው?🤝