
በዓለም የመረጃ ነፃነትን ሕገ-መንግሥታዊ እና ሕጋዊ እውቅና በመስጠት ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት ቁጥር 139 ደርሰዋል። እነዚህ ሀገራት መረጃን ለዜጎቻቸው ተደራሽ ማድረግ የመልካም አሥተዳደር እና የዴሞክራሲ መሠረት መኾኑን አምነውበት እየሠሩበት ይገኛሉ። ኢትዮጵያም የመረጃ ነፃነት ሕግን በተግባር ላይ ማዋል ከጀመረች 17 ዓመታት አልፈዋታል።
ኾኖም ባለፉት 17 ዓመታት ያገለገለው ነባሩ አዋጅ ከዘመኑ ፈጣን ተለዋዋጭነት፣ ከቴክኖሎጂ ዕድገት እና ከዜጎች ፍላጎት ጋር አብሮ መጓዝ ባለመቻሉ አዲስ አዋጅ ማርቀቅ የግድ ኾኗል።
ይህንን መነሻ በማድረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 18/2018 ዓ.ም አዲሱን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 1427/2018 አጽድቋል።
ይህንን አዋጅ አስመልክቶ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አዲሱ አዋጅ በኢትዮጵያ የመረጃ አቅርቦት እና ግልጽነት ላይ የያዛቸውን ቁልፍ ሥራዎች ግልጽ አድርጓል።
የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ አዋጁን አስመልክተው በሰጡት መግለጫቸው ላይ እንዳብራሩት ነባሩ አዋጅ መረጃን በተሟላ የአሥተዳደር ሥርዓት እና ግልጽነት ባለው አኳኋን ለማቅረብ የሚያስችሉ በርካታ የአፈጻጸም እና የአደረጃጀት ክፍተቶች ነበሩበት ብለዋል።
በአጠቃላይ 7 ክፍሎች፣ 60 አንቀጾች እና 197 ንዑስ አንቀጾችን ይዞ የጸደቀው አዲሱ አዋጅ እነዚህን የይዘት፣ የአፈጻጸም እና የአደረጃጀት ድክመቶች በመቅረፍ መረጃን ይበልጥ ተደራሽ እና ፍሰቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የአዲሱ አዋጅ ትልቁ እና ዋነኛው ማሻሻያ የመረጃ አቅርቦት ግዴታን ከመንግሥታዊ ተቋማት ወሰን የተሻገረ ማድረጉ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም መረጃ የመስጠት ግዴታ የነበረባቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና በመንግሥት ሥራ ላይ የተሰማሩ የንግድ ማኅበራት ብቻ ነበሩ።
ይህ አሠራር በግል ተቋማት ላይ የሚነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና አቤቱታዎችን ለመመርመር የዕንባ ጠባቂ ተቋም ገደብ እንዲኖረው አድርጎት ቆይቷል ነው ያሉት።
አዲሱ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 1427/2018 የግል ድርጅቶች በተለይም ከመንግሥት ጋር በጥምረት እና በጋራ በትብብር የሚሠሩት መረጃ የመስጠት ሕጋዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል ብለዋል ዋና እምባ ጠባቂዋ።
ይህ መሻሻል የግሉ ዘርፍም ተጠያቂነት እና ግልጽነት የሰፈነበት እንዲኾን ከማድረጉም በላይ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ትልቅ መሣሪያ ይኾናል ብለዋል።
ወይዘሮ ስመኝ አዲሱ አዋጅ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት ሥራቸውን በነፃነት እና ያለ ምንም ፍርሃት ማከናወን እንዲችሉ የሚያግዙ ልዩ ሕጋዊ ከለላዎችን ስለማካተቱም ነው ያብራሩት።
ይህ ማሻሻያ ሚዲያው የሕዝብ ዐይን እና ጆሮ ኾኖ የመንግሥትን እና የግል ተቋማትን አሠራር እንዲከታተል፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን እንዲያጋልጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ነው ያሉት።
ዋና ዕንባ ጠባቂዋ አክለውም ይህንን አዲስ አዋጅ ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ እና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የሚዲያው ሚና እጅግ የላቀ እንደኾነ አሳስበዋል።
ተቋሙ ይፋ ባደረገው የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርት መሠረት በዓመቱ ውስጥ 48ሺህ 189 አቤቱታ አቅራቢዎች ወደ ተቋሙ የመጡ ሲኾን፣ ከእነዚህ ውስጥ 1ሺህ 867 የሚኾኑት ትክክለኛ አቤቱታ ኾነው ተመዝግበው ተይዘዋል።
#አሚኮ #Ethiopia #እንባጠባቂ
ዘጋቢ፦ ሐናማርያም መስፍን
#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
