በፈተና ውስጥ የተዘራ የዕድገት ዘር እና የሰላም ጥም

6
💪
💧🌱
በአማራ ክልል የጸጥታ ፈተናዎች ቢኖሩም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዋል። ፕሮጀክቶቹ የተጎዳውን ማኅበረሰብ መልሰው ያቋቁማሉ፤ ምጣኔ ሀብቱን ያነቃቃሉ፤ ማኅበራዊ ትስስርንም ያጠናክራሉ። ከውድመት ላይ አዲስ ሕይወት ለመዝራት የሚደረገው ይህ የልማት እንቅስቃሴ የሕዝብ እና የመንግሥት የጽናት ማሳያ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት ተገንብቶ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ ያረፈው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከባሕር ዳር፣ ጎንደር እስከ ራስ ደጀን ያለውን ቀጣና በማስተሳሰር የሰሜን ኢትዮጵያን ቱሪዝም ያሳድጋል።
በባሕር ዳር ከተማ በ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ የተገነባው ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት የጣናን ተፈጥሯዊ ውበት ከዘመናዊ መስተንግዶ ጋር በማዋሃድ ከግጭት ይልቅ ሰላም ዋጋ እንዳለው አረጋግጧል። ይህ ሪዞርት የከተማዋን ድምቀት ይበልጥ ከማጉላቱም ባሻገር ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አዲስ ተስፋን የሰጠ ነው።
በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ በ13 ነጥብ 3 ሄክታር ላይ ያረፈው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርትም የክልሉን ተፈጥሯዊ ጸጋ በማስተዋወቅ ቱሪስቶች ለቀናት እንዲያርፉበት እና የአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ፕሮጀክቶች በሀገር ውስጥ አቅም መገንባታቸው የዕውቀት ሽግግርን ከማምጣትም በላይ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለቀጣይ ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ ናቸው።
በደብረ ማርቆስ ሕዝብ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ የጸጥታ ፈተናን ተቋቁሞ የተጠናቀቀ ነው።
ንግድን፣ ኢንቨስትመንትን እና ቱሪዝምን በማፋጠን ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ መሠረት እንደሚጥልም በምረቃው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን መሠረተ ልማት በማዘመን እና ውበትን በማላበስ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል። ልማቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከውበት እና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ገቢ በማመንጨት ለከተሞች ተጨማሪ የገቢ ምንጭም ኾነዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነትን በማረጋገጥ ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገው ጥረትም ሌላኛው ስኬት ነው። ለውጡን የተመለከቱ አርሶ አደሮችም ያለማንም ጎትጓች በልማቱ በመሳተፍ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለማዕከላዊ ገበያ አቅም እየኾኑ ይገኛሉ።
ግጭቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላውን ቢፈትነውም አላስቀረውም። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የክልሉን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አሳድገዋል፣ ምንጮች እንዲጎለብቱ እና ተጋግጠው የነበሩ መሬቶች ወደ ልማት እንዲመለሱ በማድረግ ለምርታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ወጣቶች በተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲደራጁ ዕድል በመስጠት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ያለ ስኬታማ የልማት ሥራ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።
ነባር ቅርሶችን የማደስ ሥራዎች መከናወናቸው፣ ከተማን ከገጠር እና ከተማን ከከተማ የሚያገናኙ ትልልቅ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል።
በግጭት ውስጥ ኾኖ የተገኘው ይኸው የልማት ሥራ ስኬት ክልሉ ሰላም ቢኾን ኖሮ ምን ያህል ሊያድግ እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ለጸጥታ የባከነው የሰው ኅይል፣ ጊዜ እና በጀት ወደ ትምህርት፣ ጤና እና ቴክኖሎጂ ቢዞር፣ ባለሀብቶች ያለስጋት ቢያለሙ ትልቅ ትሩፋት ይገኝ ነበር። አለመረጋጋት የዋጋ ንረትን በማባባስ ክልሉን በካፒታል እና በሰው ኀይል ፉክክር ወደኋላ ስለሚያስቀረው ሰላም የዕድገት ማፋጠኛ ሞተር እና የህልውና ጉዳይም ነው።
መንግሥት ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የልማት ሥራን በተግባር አሳይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ሁለት ዓመት ከመዋጋት ሃያ ዓመት መወያየት ይሻላል” በማለት ግጭትን በማስቀረት በውይይት ዘላቂ መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሀገርን አንድነት ለማስጠበቅ እና ትውልድን ለመታደግ፣ ሁሉም የፖለቲካ እና የማኅበረሰብ ተዋናዮች ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቧል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleነገ በኢትዮጵያ🇪🇹 አሮጌው ምዕራፍ ይዘጋል፣ አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል 🌅🤝
Next articleቤጂንግ የሻከረውን የአሜሪካ እና ኢራን ግንኙነት በማርገብ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ያላሰለሰ የዲፕሎማሲ ጥረት እንደምታደርግ ገለጸች።