
በዓለም አቀፉ የሴቶች የሰላም ቡድን እና በኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የኢትዮጵያ ሴት መሪዎች የሰላም ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ፎረሙ በዋናነት ሴቶች የሰላም ተጠቃሚ ብቻ ሳይኾኑ ሰላም ፈጣሪ እና የሰላም መሪ እንዲኾኑ ለማስቻል በጋራ የሚሠራበት ነው ተብሏል።
ፎረሙ የረጅም ግዜ አጋርነትን በማጠናከር በጋራ ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችል መኾኑም ተገልጿል።
ሰላም በትምህርት የሚጀምር በመኾኑ ዘላቂ ሰላምን በኢትዮጵያ ለመገንባት በትብብር መሥራት ይገባል ያሉት የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተወካይ አየለች እሸቴ ናቸው። ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሴት መሪዎች ሰላምን እና ዘላቂ ልማትን ማምጣት ይገባቸዋል ብለዋል።
ሴቶች በቤተሰብ መምራት፣ በግጭት አፈታት እና በማኅበረሰብ ግንባታ ያላቸውን ሚና ማስቀጠል የሚቻለው ራሳቸውን በማብቃት፣ ከግጭት እንዲጠበቁ በማድረግ እና የሰላም ተጠቃሚ እንዲኾኑ በማድረግ እንደኾነም አንስተዋል።
የፎረሙ መመስረት ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሰላም ዙሪያ ያላቸውን ልምድ ለሌሎች ሀገራት የሚያጋሩበት እና ተሞክሮ የሚወስዱበት እንደሚኾንም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
