
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መስፈን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደብረ ማርቆስ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያን በማጠናቀቁ ኩራት ይሰማዋል ብለዋል። እናንተም የዓመታት ጥያቄያችሁ ስለተፈታ እንኳን ደስ ያላችሁ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደብረ ማርቆስ ከተማ ከ50 ዓመታት በፊት ጀምሮ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አንስተዋል። በመካከል ግን የአውሮፕላን በረራ ተቋርጦ መቆየቱን እና ሕዝብ ለእንግልት ተዳርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።
ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ አድካሚ ጉዞ ያደርጉ እንደነበር እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመንገድ የሚፈጠረው ችግር ለሕዝብ ፈተና እንደነበር አንስተዋል። አሁን ግን የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ተጠናቅቆ፣ ሕዝቡም በምቾት ደኅንነቱ ተጠብቆ በመጓዝ ላይ ነው ብለዋል።
አሁን የደብረ ማርቆስ ሕዝብ ጥያቄ ተመልሷል፤ በቀን ሦስት ጊዜ፤ በሳምንት ደግሞ 21 በረራዎችን እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ለአካባቢው ኢንቨስትመንት ትልቅ እና አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር ያደርጋል ነው ያሉት። ቦይንግን ጨምሮ ትልልቅ አውሮፕላኖችን ማሳረፍ የሚችልው የአውሮፕላን ማረፉያው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደኾነበትም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን እየገነባ መኾኑንም ገልጸዋል። የሀገርን እድገት የሚያፋጥኑ ሥፍራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ግንባታው እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናም አቅርበዋል።
#ደብረ_ማርቆስ #ንጉሥ_ተክለሃይማኖት_አውሮፕላን_ማረፊያ #DebreMarqos #EthiopianAirlines #KingTeklehaimanotAirport
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ5_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
