የዋግ ኽምራን የመብራት መቆራረጥ ለመቅረፍ የኮንክሪት ምሰሶዎች ሊሠሩ ነው።

6

 

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2018 በጀት ዓመት ለመሠራት ታቅደው ግን ተቋርጠው የነበሩ የሦስት ገጠር ከተሞች የመብራት ዝርጋታ ፕሮጀክቶችን መልሶ ለመገንባት በ15 ቀናት ውስጥ የኤሌክትሪክ ምሰሶ የማጓጓዝ ሥራ እንደሚጀመር
የሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የአማራ ክልል ሪጅን አስታውቋል። የሪጅኑ ኀላፊ ኪሩቤል ከፍያለው ለአሚኮ የኽምጣና ዝግጅት ክፍል እንደገለጹት መንግሥት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን እስከ ገጠር ቀበሌዎች ለማድረስ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ኤሌክትሪክ በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ፤ በኢንዱስትሪ፣ በጤና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች አይተኬ ሚና ያለው በመኾኑ ፕሮጀክቶቹን በፍጥነት ማስቀጠል አስፈላጊ ኾኗል ነው ያሉት።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ስር በሚገኙት አካባቢዎች ማለትም፦
👉 በስሃላ ሰየምት (ግርማይቱ ዋለ)፣
👉 በዝቋላ (አደን ዲግና) እና
👉 በድሃና ወረዳ (ጎመንጌ ጥንስስ) የከተማ ማዕከላት
በ2018 በጀት ዓመት አዲስ የመብራት ዝርጋታ ለማካሄድ ለተለያዩ ተቋራጮች በጨረታ ተሰጥቶ የነበረ ቢኾንም ከነዳጅ አቅርቦት ችግር ጋር ተያይዞ ተቋራጮቹ “አዋጭ አይደለም” በሚል ሰበብ ሥራቸውን አቋርጠው ወጥተው እንደነበርም አስታውሰዋል። ይህም በጉጉት ይጠብቅ በነበረው ማኅበረሰብ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ እንደነበር ነው የገለጹት።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሪጅኑ ተቋራጮችን ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ አቅም ለመሥራት መወሰኑን እና ከኤሌክትሪክ ምሰሶ አምራቾች ጋር የውል ስምምነት ማድረጉን ጠቁመዋል።

በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ ምሰሶዎችን የማጓጓዝ ሥራ በይፋ ይጀመራል ነው ያሉት።

የተከዜ ድልድይ ስጋትን በተመለከተም መሸከም የሚችለውን ያህል የምሰሶ መጠን ስለምናመላልስ ይህ ጉዳይ ለሪጅኑ የሚያሳስብ ፈተና አይደለም ሲሉ ኀላፊው አረጋግጠዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያለበት አካባቢ ቢኾንም እንኳ በቂ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ኢንቨስትመንቱ እንዲቀዛቀዝ አድርጎት እንደቆየም አስታውሰዋል።

ይህንን በተደጋጋሚ ለንፋስ እና ለስርቆት የሚጋለጠውን የብረት ምሰሶ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ በቀላሉ የማይበገሩ የኮንክሪት ምሰሶዎችን መተካት እንደ አዋጭ መፍትሔ ተወስዶ እየተሠራበት እንደሚገኝም አቶ ኪሩቤል ከፍያለው ገልጸዋል።

#ዋግኽምራ #ሰቆጣ #አማራክልል #ዋግኽምራ_ልማት #አሚኮጸነኸነመኗነኗኗኗ #ባሕር_ዳር #ሐምሌ5_2018_ዓ_ም

በኪሮስ ወልደ ተንሣይ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከታሪካዊ ጠላቶች እስከ ውስጣዊ ባንዳዎች፤ የጽምዶ ሴራ እና የኢትዮጵያ ዝግጁነት
Next article“ኢትዮጵያ እየመከረች ነው” የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ።