ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ሌሎች የደኅንነት ስጋቶችን ለመከላከል በትኩረት እየሠራች ነው።

4

 

ዓለም አቀፍ የፓርላማ የመረጃ እና ደኅንነት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጉባኤው በሀገራት መካከል ስልታዊ አጋርነትን እና ትስስር በመፍጠር ወቅታዊ ዓለማቀፋዊ ስጋቶችን በጋራ ለማለፍ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል።

መድረኩ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የታየበትን ምርጫ ባካሄደችበት ወቅት መደረጉ አስደሳች መኾኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና መሰል የደኅንነት ስጋቶችን ለመከላከል በትኩረት እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የጤና ሥጋቶችን እና ወረርሽኝኞችን ለመከላከል፤ የምግብ ደኅንነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራች ነው ብለዋል።

በዓለም ላይ ሥጋት እየኾነ የመጣውን የሳይበር ደኅንነት ሥጋት ለመቆጣጠር የሚያግዙ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎችን በመተግበር ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።

ይህ ፎረም በዓለም ላይ ሥጋት የኾኑ ጉዳዮችን በጋራ ለመፍታት በፓርላሜንታሪያን ፖሊሲ አውጪዎች፣ በምሁራን እና በአጋሮች መካከል ልምድን ለመለዋወጥ እና ቀጣይነት ያለው አጋርነት ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በጉባኤው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወከሉ የምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የደኅንነት ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

#ዓለምአቀፍጉባኤ #የመረጃደኅንነትን #ለማስጠበቅ

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ3_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበዘንድሮው የአልማ ሳምንት ሰፊ ሃብት ለማሠባሠብ ታቅዷል።