
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያለፈውን የለውጥ ጉዞ ስኬታማነት እና የአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት እና ራዕይን በተመለከተ ከሠራተኞቹ ጋር ትውውቅ አካሂዷል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ በመድረኩ ላይ በ2018 በጀት ዓመት አበረታች እና ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል። ሠራተኞች በአዲሱ በጀት ዓመት ትናንት የነበረውን አሠራር በማሳደግ በቀጣዩ በጀት ዓመት ከትናንቱ የተሻለ ተዕጽኖ ፈጣሪ ተቋም ለማድረግ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በ2019 በጀት ዓመት የላቀ እና ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ አዳዲስ የትኩረት አቅጣጫዎች መለየታቸውንም አስታውቀዋል።
ውጤታማነት በመድከም ብቻ አይመጣም ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው፣ አዲሱ ዓመት ሥራዎች በከፍተኛ ጥራት የሚከናወኑበት እና ማኅበረሰባዊ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ እንዲኾኑ አስቦ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ዋና ሥራ አሥፈጻሚው የአሚኮ ተመራጭነት በቀጥታ የሚለካው በሠራተኞቹ የሥራ ውጤት ላይ በመኾኑ ማንኛውም ዘገባ ጥራትን እና የሕዝብ ለውጥን ታሳቢ ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ተቋሙን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሀብትን በቁጠባ እና በውጤታማነት መጠቀም፣ ጊዜን ጨምሮ ማንኛውንም አይነት የሀብት ብክነትን አጥብቆ መጸየፍ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ሠራተኞችም ዕውቀት እና ክህሎታቸውን በማሳደግ የአሚኮን ተመራጭነት ማላቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። አሚኮን በብራንዲንግ፣ በገጽታ ግንባታ እና በዘላቂ አጋርነት ከፍታውን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራልም ነው ያሉት።
መረጃዎችን ለተመልካች ይበልጥ በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እና የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
አሚኮን ስታንዳርድ ያለው ዘመናዊ ተቋም ለማድረግም በሥራ፣ በአለባበስ እና በሌሎችም አሠራሮች ላይ የላቀ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከሁሉም የአሚኮ ቤተሰብ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በቅርቡም አዲስ የልጆች ቻናል ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደኾነም አብራርተዋል። እያንዳንዱ ሠራተኛ ዕውቀቱን እና ክህሎቱን ለዚህ አዲስ ጅማሮ እንዲያበረክትም አስገንዝበዋል።
አሚኮ ክልላዊና ሀገራዊ ተደራሽነቱን በፍጥነት እያሳደግ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙሉቀን በዚህ ረገድ ተይዘው እየተካናወኑ የሚገኙ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ስኬታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህን ታላላቅ ግቦች ለማሳካት ሥራዎችን በዕቅድ መምራት እና ችግር ፈቺ አመራርን መገንባት ብሎም ጠንካራ ተቋማዊ የቤተሰብ ባሕልን ማዳበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
