
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 29/2018 ዓ.ም
ሕወሓት የመንግሥት ሥልጣንን ተቆጣጥሮ በነበረበት ዓመታት በበርካታ ወገኖች እና ተቋማት ላይ ታሪክ የማይሽረው ጥፋቶችን ፈጽሟል። ዜጎችን ለከፋ ሰብዓዊ መብት ረገጣ፤ ሀገሪቱንም ለኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ዳርጓል።
ቡድኑ አሁንም ድረስ ከታሪኩ የማይማር እና ለጥፋት የተፈጠረ ስለመኾኑ የተለያዩ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ይገልጻሉ።
በአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ፖሊሲ እና አመራር መምህር እና ተመራማሪ ደስታው አማረ (ዶ.ር) እንደገለጹት ሕወሓት በሚከተለው ኋላቀር የፖለቲካ አካሄድ ከኢትዮጵያ ባሕል እና እሴት ያፈነገጠ መጠነ ሰፊ ጥፋቶችን ፈጽሟል።
ከምስረታው ጀምሮ ጸብ አጫሪ እና ግትር ባህሪ ያለው፣ በውጭ ጠላቶች የሚዘወር፣ በባዕድ የጥፋት ሰነዶች የተጠመቀ እና ራሱንም “ከጨቋኝ ተጨቋኝ” የሀሰት ትርክት ማላቀቅ ያልቻለ ቡድን ስለመኾኑም ያስረዳሉ።
በሕዝቦች መካከል የጥርጣሬ መርዝ በመርጨት ብሔራዊ እሴቶቻችንን ለመሸርሸር ሥርዓታዊ ቅርጽ አስይዞ ሢሠራ ቆይቷል።
በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋሻ እና መከታ የኾነውን የመከላከያ ሠራዊት በመክዳት የፈጸመው ጥቃት ታሪክ የማይሽረው የጭካኔው ማሳያ ነው ብለዋል።
በአንጻሩ መንግሥት በሆደሰፊነት ለዘላቂ ሰላም ያለውን አቋም በተለያየ ወቅት አሳይቷል። ለዚህም የሰላም ጥሪዎችን በማድረግ፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ታጣቂዎችን መልሶ በመቀላቀል (የዲዲአር መርሐግብር) እና የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን በአብነት ያነሳሉ።
ነገር ግን ሕወሓት ይህንን ሁሉ አማራጭ በመተው አሁንም በጸብ አጫሪነቱ ቀጥሎ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። አስገዳጅ የጦርነት አዋጅ እስከማውጣት እና ወጣቶችን እስከማፈስ የደረሰ ዝግጅት እያደረገ መኾኑንም አመላክተዋል።
ይህ አካሄድ ፈጽሞ ተገቢ አለመኾኑንም ይመክራሉ። የትግራይ ሕዝብም ያለፈውን ሰቆቃ በማስታወስ በቃህ ሊለው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
መንግሥት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ እና የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር፣ አሉ የሚባሉ ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል።
የሕወሓት መሥራች የነበሩት አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) የሕወሓት መሪዎች በግል ጥቅም የተሠባሠቡ ለጥቅማቸው እና ለሥልጣናቸው ብቻ የቆሙ በመኾናቸው ለአሁኑ ምስቅልቅል ምክንያት ኾነዋል ይላሉ።
ቡድኑ መንግሥት ለሚያቀርበው የሰላም ጥረት ዝግጁ እንዳልኾነም ጠቁመዋል። ይባስ ብሎ ሕጻናትን ጨምሮ በግዳጅ በመመልመል ለጦርነት እየተዘጋጀ ስለመኾኑም አንስተዋል።
ዓለምዓቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን ሕገ ወጥ ቡድን ከድርጊቱ ሊያስቆመው እና ሊያወግዘው እንደሚገባም ተናግረዋል! 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
