🏘️ ከሃሳብ ወደ ተግባር የኢትዮጵያ የገጠር ኮሪደር ልማት! 🇪🇹

4

 

#ባሕር_ዳር: ሰኔ 27/2018 ዓ.ም የጥንታዊ ሥልጣኔ ማሕጸን፤ ዘመናትን በጽናት ያሳለፈች፣ ማንነቷን ጠብቃ የዘለቀች ታሪካዊ ሀገር ናት ኢትዮጵያ ።

በየዘመኑ የገጠሟትን ፈተናዎች በጽናት እያለፈች፤ የትናንቱን የክብር ዘመን ለመድገም ወደ ከፍታዋ እየተጓዘች ያለች፤ የብልጽግና ጉዞዋን በቁርጠኝነት እያፋጠነች የምትገኝ ናት።

የአክሱም ሐውልቶች ዘመን አይሽሬ የኢንጂነሪንግ ጥበብ፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጀጎል ግንብ የኪነ-ሕንጻ ጥበቦች የትናንቷ ከፍታ ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ የጥበብ ማማዎች፣ የዘመናት ፈተናዎችን ተቋቁመው ዓለምን ያስደነቁ የኢትዮጵያ ታላቅነት ያሳዩ ምስክሮች ናቸው።

ዛሬም ቢኾን የትናንቱን ታሪክ ከነገ የብልጽግና ተስፋ ጋር የሚያስተሳስር እና የሚያገምድ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት እየተተገበረ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ፤ የሥልጣኔ ባለቤት የኾነውን የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለመቀየር እና የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ መሠረት ለማጽናት እየተከናወነ ያለ ወሳኝ እርምጃ ነው።

ይህ የልማት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን የጥንት አኩሪ ታሪክ በዘመናዊ እውቀት እና ቴክኖሎጂ በማዘመን ለተሻለ ነገ ለማሻገር ያለመ ነው። ኢትዮጵያ አቅዳ በመፈጸም፤ አልማ የማሳካት ራዕዩን እውን በማድረግ ትልልቅ ሜጋ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ እያስመሰከረች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ አቅዶ የመፈጸም ባሕልን እያዳበረች የብልጽግና ራዕይዋን በተጨባጭ ምድር ላይ እውን እያደረገች ነው። ሀገሪቱ እያከናወነች የምትገኘው ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ የሚያሳዩ የታሪክ አሻራዎች ኾነዋል።

በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ዘመናዊ እና ምቹ የኑሮ ደረጃን በመፍጠር የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘዴ ለማሻሻል ሰፊ ሀገራዊ እንቅስቃሴንም ጀምራለች።

ይህ የገጠር ማሻሻያ ሥራ አርሶ አደሮችን በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ እርምጃ ነው። ይህም አነስተኛ ወጪ በሚጠይቁ፤ በአካባቢው ግብዓቶች የሚገነቡ፤ ነገር ግን ምቹ እና ሞዴል በኾኑ መኖሪያ ቤቶች የአርሶ አደሮችን ሕይወት መለወጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት የገጠር ኮሪደር ልማት ዘመናዊ የእንስሳት ማደሪያዎች፤ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ባዮ ጋዝን በማሟላት ለሕይወት ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችል ነው ። በጓሮ የሌማት ቱርፋትን በማልማት የዜጎችን አመጋገብ ማሻሻል እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደኾነ ነው ያስረዱት።

​ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት “እኛ አንችልም” የሚለውን የተሳሳተ የአስተሳሰብ ስብራት በመስበር በራስ አቅም የመልማት እና በራስ መተማመንን መገንባት ያስቻለ ነውም ብለዋል።

​በሀገር አቀፍ ደረጃ የታቀደውን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቤቶችን ግንባታ ለማሳካት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ዘመናዊ ከተሞችን እና መንደሮችን የመገንባት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው።
“ጸዳ ያለ እና የዜጎቻችንን ኑሮ የሚያዘምኑ ቤቶችን ማብዛት ይኖርብናል” ነው ያሉት። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድንኾን ያስችላል ብለዋል።

“ጀግንነት በጦር መሳሪያ ሳይኾን በድኾች ቤት መለወጥ እና ሀገርን በማልማት ይለካል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነተኛ ተግባር በቃል ሳይኾን በሥራ የሚረጋገጥ መኾኑን ጠቁመዋል። የነገዋን የለመለመች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

​የምንገነባው ሀገር የየዕለት ውሏችን ውጤት ነው! 🇪🇹

እርስዎስ ይህን ለውጥ እንዴት ይመለከቱታል ?

በሥራውድንቅ ደሳለው

​#ኢትዮጵያ#RuralCorridor
Development#የአርሶአደር ለውጥ#በራስመተማመን#FutureEthiopia#

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየገጠር ኮሪደር ልማት ለአርሶ አደሩ ሁለንተናዊ የኑሮ ሽግግር 🚜🏡
Next articleየ40 ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ላሊበላን ጎብኝተዋል።