💻🏢በክልሉ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ኮምፒውተሮች ተሰራጩ።

13

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ኮምፒውተሮችን ለዞኖች እና ለከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያዎች ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፉ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ደ.ር) ዘላቂ የኢኮኖሚ ግንባታን ለማረጋገጥ እና ሰላምን ለማጽናት በዕውቀት የለማ የሰው ኀይል መገንባት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በጽናት መሻገር የሚችሉ እና ዘመኑን የዋጁ ዜጎችን ማፍራት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት። መንግሥት ነገን አስቦ እየሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።

​የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እና ትምህርትን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኅላፊ ጥላሁን ወርቅነህ
የጸጥታ ችግሮች በትምህርት ዘርፉ ላይ ፈተና ቢኾኑም ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የትምህርት ግብዓቶችን ለማሟላት ታቅዶ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።

​የትምህርት ሥርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን እና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ 2ሺህ 135 ኮምፒውተሮች ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት።

በቀጣይም ቴክኖሎጂውን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አስረድተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኅላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) ድጋፉ የሚሰጠውን የኦንላይን ፈተና ስኬታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል። ድጋፉ ቁልፍ ችግሮችን የፈታ ነው፤ ብቁ ትውልድ ለማፍራትም ያግዛል ነው ያሉት።

​የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኅላፊ
የሺወርቅ ድረስ ክልሉ ያደረገው ድጋፍ የነበረውን የኮምፒውተር እጥረት የሚቀርፍ እና በኦንላይን ፈተና ለመስጠት ለሚደረገው ዝግጅት በትክክለኛው ጊዜ የደረሰ ትልቅ ግብዓት ነው ብለዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም አመሥግነዋል።

#አሚኮ_ዜና #የትምህርት_ቁሳቁስ #ድጋፍ #ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየኢድ አል አደሃ በዓል መታዘዝን በተግባር ያስተማረ ነው።
Next article“በቦረና እየተገነባ ያለው ግዙፉ የውኃ ፕሮጀክት የነዋሪዎችን ሕይወት እየቀየረ ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)