“ዘመናትን የተሻገረ የማኅበረሰቡ አብሮነት ለዛሬዋ የጎንደር ከፍታ ዋነኛ መሠረት ኾኗል” አቶ ቻላቸው ዳኘው

9

 

ጎንደር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 447ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በጎንደር ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የአረፋ በዓል ታላቅ የመስዋትነት፣ የፍጹም ታማኝነት እና የጽናት ማሳያ መኾኑን ተናግረዋል።

ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በዓሉን ሲያከብር በከተማዋ ለዘመናት የዘለቀውን የመተሳሰብ እሴት መሠረት በማድረግ የተቸገሩትን በመደገፍ፣ ማዕድ በማጋራት፣ አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

“ዘመናችን የተሻገረ የማኅበረሰቡ አብሮነት ለዛሬዋ የጎንደር ከፍታ ዋነኛ መሠረት ኾኗል” ነው ያሉት። ለዘላቂ ሰላም ያለው የማይናወጥ ጽናትም ዛሬ ከተማዋ ለደረሰችበት የልማት ውጤት ሚናው ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።

በከተማዋ እየተከናወኑ ላሉት የልማት ሥራዎች የሙስሊሙ ማኅበረሰብ እና የመላው ነዋሪ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ስለመኾኑም አንስተዋል። በቀጣይም የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሀሰን ደሴ (ዶ.ር) እንደገለጹት የዒድ አል አድሃ በዓል በእስልምና ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ትርጉም ያለው በዓል ነው።

በሰው ልጆች መካከል የዘር፣ የቀለም እና የሀብት ልዩነት ሳይኖር በፈጣሪ ዘንድ እኩል መኾናቸውን የሚያሳይ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት። እንደ ነቢዩ ኢብራሂም ሁሉ እኛም ለሀገራችን ሰላም እና ለሕዝባችን አንድነት በቁርጠኝነት ልንተጋ ይገባል ነው ያሉት።

በዓሉ የደስታ ብቻ ሳይኾን የተቸገሩትን፣ ወላጅ አልባ ሕጻናትን እና አቅመ ደካሞችን በማሰብ አብሮነትን የምናሳይበት ልዩ ቀን ነው ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #ዓረፋ #ዒድ_አል_አደሃ #ጎንደር #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልእክት
Next articleበዓሉን ለሀገር ሰላም እና አንድነት በመጸለይ ማክበር ይገባል።