
ደባርቅ: ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ እና የምርጫ ቅስቀሳ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ተካሂዷል።
በሰልፉ በየደረጃው ያሉ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች እና የፓርቲው ደጋፊዎች ተሳትፈዋል።
በድጋፍ ሰልፍ መርሐ ግብሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ዕውቅና የሚሰጡ የተለያዩ መሪ መልዕክቶች ተደምጠዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አማካሪ ደብረወርቅ ይግዛው ብልጽግና ፓርቲ የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ፓርቲው በቀጣይም የማኅበረሰቡን ሕይዎት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናዎን ቁርጠኛ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አማረ ጎሹ ምርጫ ከፖለቲካዊ ውድድር ባለፈ የሀገርን መጻዒ ዕድል የሚወስን በመኾኑ ትኩረት ሰጥቶ ሂደቱን መከዎን እንደሚገባ ገልጸዋል።
አንድነት ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት አሰፈላጊ በመኾኑ በጋራ መቆም እና ኅብረብሔራዊነትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የሀገር ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥቶ በመሥራት የተሻለ የውጭ ግንኙነት ሂደት መፈጠሩንም አብራርተዋል።
የደባርቅ ከተማ ከንቲባ ጌትነት ጸጋዬ በዲጂታላይዜሽን፣ በትምህርት፣ በጤና እና በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፎች የተሻሉ ተግባራት መከናዎናቸውን አስታውሰዋል።
እንደሠለጠነ ማኅበረሰብ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ምርጫ የዳበረ የዴሞክራሲ መገለጫ በመኾኑ ይወክለኛል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
