
አዲስ አበባ: ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ አድርጓል።
በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ እና በምርጫ ቅስቀሳው የፓርቲው ደጋፊዎች እና ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ ብልጽግና ፓርቲ በከተማዋ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራ መሠራቱን አስታውሰዋል።
ብልጽግና በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካሸነፈ የጀመራቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ለማሳካት እንደሚተጋ ቃል ገብተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ብልጽግና የገባውን ቃል የፈጸመ የተግባር ፓርቲ ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ፈጣን እና ቀልጣፋ ለማድረግ እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም በምርጫው ብልጽግና ፓርቲ ካሸነፈ አዲስ አበባን በዲጂታል ያደገች ከተማ ከማድረግ በተጨማሪ አምራች ከተማ ለማድረግ ፓርቲው ይሠራል ብለዋል።
በከተማዋ የመሠረተ ልማት ሥራዎች አሁን ካሉበት በማሻሻል የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሠራ ለፓርቲው ደጋፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
