“ኢትዮጵያ ለመመለስ እየሠራች ያለችው ሕልውናዋን ነው” የፖለቲካ ተንታኝ

4
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ያዕቆብ ኀይለማርያም (ዶ.ር) አሰብ የማን ናት? በሚለው መጽሐፋቸው የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን በእጥፍ ለማሳደግ 24 ዓመታትን እንደሚወስድባቸው ጥናቶችን መሠረት አድርገው ጽፈዋል።
በአንጻሩ መውጫ እና መግቢያ የሌላቸው ሀገራት ደግሞ 36 ዓመታትን እንደሚፈጅባቸው አትተዋል። የባሕር በር ለአንዲት ሀገር መጻኢ እጣ ፈንታ የሚወስን እንደኾነ በመጽሐፋቸው ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተመራማሪ እና ተንታኝ ሚካኤል ማስሬ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በፍትሐዊ ንግግር እና በዲፕሎማሲ መውጫ የማግኘት ዕድሉ እንዳላቸው ዓለም አቀፍ ሕጉ ይደነግጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለማግኘት እየጣረች ያለችው ሕልውናዋን እንደኾነም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ካሻት በዲፕሎማሲ አሊያም ዓለም አቀፍ ሕጉን ተከትላ ከሄደች የባሕር በር ባለቤት የማትኾንበት ዕድል አይኖርም ነው ያሉት። ብልሃት የተሞላበት ዲፕሎማሲን አጠናክራ ከቀጠለች መንገዷ ይቀልላታልም ብለዋል።
ሰጥቶ የመቀበልን መርሕ መሠረት ያደረገ ኢኮኖሚያዊ ትስስር መፍጠርም የባሕር በር ለማግኘት አንዱ አማራጭ መኾኑን ገልጸዋል። ያ ካልተሳካ ግን ፍትሕን ፍለጋ ላይ መንቀሳቀስ ያስፈልጋታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ሃብቷ የነበረውን ቀይ ባሕር በማጣቷ የንግድ እንቅስቃሴዋ በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዲኾን አድርጓታል ብለዋል።
ይህ መኾኑም በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 6 እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ለወደብ ኪራይ እንድትከፍል ኾናለች ነው ያሉት።
ሀገሪቱ ቀይ ባሕርን ያጣችው በወቅቱ በነበረ ፖለቲካዊ ፍላጎት ስለነበረ እንደገና የማይታይበት ጉዳይ አይኖርም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚ ብትኾን የመጀመሪያዋ ተጠቃሚ ሀገር ኤርትራ ናት ይላሉ። ለዚህም “ኤርትራ የአሰብ ወደብን ከያዘች ጀምሮ የግመሎች ማጠጫ አደረገችው እንጅ አልተጠቀመችበትም” ብለዋል። በጋራ መለወጥን መለማመድ አለባት ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረቱ ግብርና ይሁን እንጅ የለውጥ ቁልፉ ግን ያለው የባሕር በር ላይ እንደኾነም አንስተዋል። ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ምርት መመረት ብቻውን በቂ እንዳልኾነም ጠቁመዋል።
ጅቡቲ ላይ ከ12 በላይ የኾኑ ሀገራት የጦር ቤዛቸውን የማስቀመጥ ምስጢራቸው እና የኀያላን ሀገራት ዐይን ማረፊያ ለመኾኗ ምክንያቱ የባሕር በር ባለቤት መኾኗ ነው ብለዋል። የባሕ በር ባለቤት ስትኾን ሁሉም ሀገራት ይፈልጉሀል ነው ያሉት።
የቀይ ባሕር ጉዳይ በቀጣናው የጅኦ ፖለቲካ ፉክክር ላይ ትልቅ ሚዛን ነው ብለዋል። የባሕር በር የጂኦ ፖለቲካ መዘወሪያ ቁልፍ መሣሪያ እንደኾነም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ካለው ዕድገት አንጻር የሚያስፈልገው መውጫ እና መግቢያ በር ነው ብለዋል። ይህ የሀገር መሻት ግን ዳር እንዲደርስ የሕዝብ ድጋፍ እና እገዛ ያስፈልገዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየልብ ሕመም ይድናል ?
Next articleየጠላትን ሴራ በጋራ መታገል ይገባል።