
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦፕቶሜትሪ ባለሙያዎች ማኅበር 41ኛውን ዓለም አቀፍ እና 11ኛውን ሀገር አቀፍ የዐይን ጤና ሳምንት ምክንያት በማድረግ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በመገኘት ለሠራተኞች የዐይን ምርመራ እና የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል።
የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ሙሉሰው ተገኘ መርሐ ግብሩ ስለ ሙያው ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ኅብረተሰቡ ስለ ዐይን ጤናው ያለውንተ ዕውቀት ለማሳደግ እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።
ከዕይታ ልኬት እና ከዐይን ግፊት ምርመራ በተጨማሪ እንደ አስፈላጊነቱ የመነጽር እና የመድኃኒት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ በዲጂታል መሣሪያዎች እና በጨረር ተጋላጭነት ምክንያት የዐይን ጤና ከዕድሜ በፊት ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የኾኑ ሰዎች በዓመት አንድ ጊዜ፣ ከ18 እስከ 40 ዓመት የኾኑ ደግሞ በየሁለት ዓመቱ ምርመራ እንዲያደርጉ ሙያዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ኅዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር
ጋዜጠኛ መሠረት አስማረ የአሚኮ ሠራተኞች የሥራ ተፈጥሮ ከዲጂታል መሣሪያዎች እና ከኮምፒውተር ጋር የቀጥታ ግንኙነት ያለው በመኾኑ ለዐይን ጤና ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የሠራተኞች ጤና ይቀድማል በሚል መርሕ ዓመታዊ የዐይን ጤና ምርመራ እንዲያገኙ እያደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል። መርሐ ግብሩ ሠራተኛው ስለ ዐይኑ ጤና ትኩረት እንዲሰጥ ማንቂያ ደወል እንደሚኾንም ተናግረዋል።
አሚኮ ከአጋር አካላት ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በመጠቀም እንዲህ ያሉ የጤና ድጋፎችን እና ሙያዊ ሥልጠናዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አገልግሎቱን ያገኙ የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎችም በሥራ ጫና ምክንያት ወደ ሕክምና ተቋማት ሄዶ ለመታየት ጊዜ እንደሚያጥራቸው ተናግረዋል። ምርመራው በሥራ ቦታቸው መከናወኑ ጊዜያቸውን ከመቆጠብ ባለፈ ለጤናቸው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው የገለጹት።
የዕይታ ችግር ላለባቸው ሠራተኞች የሕክምና መነጸሮች መለገሳቸው በሥራ ገበታ ላይ ለሚገጥም የዕይታ መጋረድ ትልቅ አቅም እንደሚኾንም ጠቅሰዋል።
እንዲህ ዓይነቱ የጤና ድጋፍ ሠራተኛው በጤናው ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ በመረዳት የመፍትሔ አካል እንዲኾን እና በሙሉ አቅሙ ሥራውን እንዲያከናውን የሚያበረታታ መኾኑም ገልጸዋል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
