
አዲስ አበባ: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሰጠው ልዩ ትኩረት እና ድጋፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ከማሳደጉ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያድግ ማስቻሉን አምራቾች ገልጸዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ የሚገኙ የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ፣ የምግብ እና የኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶች አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በምልከታው ወቅት የተለያዩ ፋብሪካዎች የሥራ ኀላፊዎች ከመንግሥት የሚደረግላቸው ድጋፍ ለውጤታማነታቸው ቁልፍ መኾኑን ገልጸዋል።
የኒው ዊንግ አዲስ ጫማ እና ቆዳ ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ኢቫኖ መስፍን እንደገለጹት ድርጅቱ ለ16 ዓመታት በዘርፉ ቢቆይም ቀደም ባሉት ዓመታት ይደረግለት የነበረው ድጋፍ ዝቅተኛ በመኾኑ ውጤታማ አልነበረም።
በአሁኑ ወቅት ግን በመንግሥት በኩል ለላኪዎች በሚደረገው የፋይናንስ እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ምርቶቻቸውን ለሰሜን አሜሪካ ገበያ በስፋት ማቅረብ እና ከዓለም ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር መወዳደር መቻላቸውን አስረድተዋል።
የቡም ማኑፋክቸሪንግ ሥራ አሥኪያጅ ጸጋ ደበበ እንደገለጹት ድርጅቱ የተለያዩ ማቀዝቀዣዎችን በማምረት የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እየተካ ይገኛል።
መንግሥት የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት እና ለማስፋፊያ የሚኾን መሬት በማመቻቸት ባደረገው ድጋፍ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል። ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ውስጥም ለ400 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ዘርፉ ለኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡም በምልከታው ተገልጿል።
ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ ውጭ ገቢያ በሚላኩ ምርቶች እየተገኘ የሚገኘው ገቢ እያደገ መጥቷል።
መንግሥት በተለይ ተኪ ምርትን በማሳደግ እና ለላኪዎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እያደረገ ያለው ድጋፍ ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥም ኾነ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያሳድጉ ትልቅ አቅም መኾኑ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
