
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ባንክ እና ቪዛ ኩባንያ በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ለማፋጠን የሚያስችል የስትራቴጂያዊ ዕድገት ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል።
ይህ አጋርነት ባንኩ የቪዛን ዓለም አቀፍ አውታረ መረብ እና የቴክኖሎጂ ልምድ በመጠቀም የካርድ አቅርቦቱን እንዲያስፋፋ እና ዘመናዊ የክፍያ መሠረተ ልማት እንዲገነባ የሚያስችለው ነው።
በስምምነቱ መሠረት አማራ ባንክ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የቪዛ ቅድመ ክፍያ ክላሲክ፣ ጎልድ፣ ፕላቲኒየም ካርዶችን እና የዴቢት ካርድ አማራጮችን ለደንበኞቹ ማቅረብ ይጀምራል ተብሏል።
ይህ አሠራር ደንበኞች በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የክፍያ መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ ዕድል ይፈጥራል።
ከካርድ አቅርቦት ባለፈ፣ ቪዛ ለአማራ ባንክ ስትራቴጂያዊ የማማከር አገልግሎት፣ የማጭበርበር ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የክትትል መሣሪያዎች እና የፕሮጀክት አመራር ድጋፍ ይሰጣል።
ይህም የባንኩ ደንበኞች ከፍተኛውን የደኅንነት ደረጃ የጠበቀ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
የአማራ ባንክ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ እሸቴ የማታ እንደገለጹት ይህ ስምምነት ባንኩ በዲጂታል ክፍያ ዘርፍ ቀዳሚ ለመኾን ለሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
የቪዛን ቴክኖሎጂ ማዋሃድ ደንበኞች ወደ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እንዲቀላቀሉ ከማገዙም በላይ የኢትዮጵያን የጥሬ ገንዘብ አልባ ማኅበረሰብ ሽግግር እና ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳን ለማሳካት ትልቅ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
የቪዛ የምሥራቅ አፍሪካ ካንትሪ ዳይሬክተር ያሬድ እንዳለ ቪዛ በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ዕድገትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መኾኑን ገልጸዋል። ከአማራ ባንክ ጋር የተመሠረተው ትብብር የባንኩን የፈጠራ አቅም እና የአደጋ ስጋት የመቆጣጠር ብቃት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።
አማራ ባንክ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ ነው። ይህ አዲስ አጋርነት ባንኩ ተደራሽነቱን በማስፋት ለግለሰቦች እና ለንግድ ተቋማት ሳምንቱን ሙሉ አስተማማኝ የክፍያ አማራጮችን ለማቅረብ ያስችለዋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
