
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ተኪ ምርት የማሸጋገር እና የዘርፉን ምርታማነት የማሳደግ ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መኾኑን የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አዲሴ መብራቴ ቢሮው ስትራቴጂካዊ ዝግጅቶችን እና የምሁራን ጥናትን መሠረት በማድረግ ነባር ኢንዱስትሪዎች ወደ ተኪ ምርት እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 463 አምራቾች ተኪ ምርት ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል። ይህም በበጀት ዓመቱ 400 ኢንዱስትሪዎችን ለማሸጋገር ከተያዘው ዕቅድ በላይ መኾኑን ገልጸዋል።
በምርት መጠንም የታቀደውን 306 ሺህ 810 ቶን በማለፍ 366 ሺህ 407 ቶን ምርት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
በተኪ ምርት አምራች ኢንዱስትሪዎች የታየው ከፍተኛ የምርት ዕድገት ኢትዮጵያ ለውጭ ምርቶች ልታወጣ የነበረውን 469 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ማስቻሉን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 59 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ ወደ 62 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የዩኒሰን የምግብ ዘይት ፋብሪካም ተኪ ምርት በማምረት ገበያውን የማረጋጋት እና የውጭ ምንዛሪ የማዳን አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ገልጸዋል።
ፋብሪካው በቀን 600 ኩንታል የቅባት እህሎችን የመጭመቅ እና 60 ሺህ ሊትር ዘይት የማጣራት አቅም ያለው መኾኑን የፋብሪካው ሥራ አሥኪያጁ ዳዊት ታረቀኝ ተናግረዋል።
ፋብሪካው አስፈላጊ ግብዓቶችንም ሙሉ በሙሉ ከሀገር ውስጥ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን እያዳነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የምርት ጥራት እና የዋጋ ተመጣጣኝነት ለድርድር የማይቀርቡ ጉዳዮች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ከተማ በሦስት ቅርንጫፎች በተመጣጣኝ ዋጋ በቀጥታ ለተጠቃሚው እያደረሰ መኾኑን ተናግረዋል።
ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገው ጥረት ይበልጥ እንዲጠናከር የግብዓት ትስስር እና አቅርቦትን ማጠናከር፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እና በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ተከታታይነት ያለው የሙያ ድጋፍ እና ክትትል ማካሄድ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮው አስታውቋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
