የኢድ አልፈጥር በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

24

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢድ አልፈጥር በዓል በመላው የክልሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በፍቅር እና በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን እና ሕዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የኢድ አልፈጥር
በዓል ከመንፈሳዊነቱ ባለፈ የአንድነት፣ የመከባበር እና የመረዳዳት እሴቶች በተንጸባረቁበት መንገድ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የኢድ ሶላት በሚከናወንባቸው መስጊዶች እና አደባባዮች ላይ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ ግብረ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ይሠራል ነው ያሉት። ከመቼውም ጊዜ የተለየ ሁኔታ የተቀናጀ ስምሪት በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱንም አስታውቀዋል።

የኢድ አልፈጥር በዓል የአንድነታችን ውበት እና የመተሳሰባችን መገለጫ ነው ብለዋል።

በዓሉን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን የጸጥታ ኃይሉ በልዩ ትኩረት እየተከታተለ ይገኛል ነው ያሉት። ማንኛውንም የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚያውኩ ተግባራት ላይ የጸጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ሙሉ ዝግጅት ላይ መኾኑን ተናግረዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ ያለምንም ችግር በዓሉን እንዲያከብር የጸጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን ጥበቃ ሁሉ ያከናውናል ነው ያሉት። በበዓል ሰሞን የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ከኅብረተሰቡ ጋር በቅርበት እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በበዓሉ ዕለት የሰዎች እና የተሽከርካሪዎችን ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር እና አደጋ እንዳይደርስ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በልዩ ትኩረት እንደሚሠማሩም ጠቁመዋል።

ሰላም የጋራ እሴት መኾኑን የጠቀሱት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ኅብረተሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ማንኛውንም አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥሙ በአቅራቢያ ለሚገኝ የጸጥታ አካል ጥቆማ በመስጠት ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲኾንም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጨረቃ ዛሬ ከታየች የኢድ አልፈጥር በዓል ነገ ካልታየች ደግሞ ከነገ ወዲያ ይኾናል።
Next articleኮሌራ እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከል ይገባል።