“ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

32

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ እና በኤኤምጂ (AMG) – እንዶዴ የባቡር መሥመር ፕሮጀክቶች ጉብኝት አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነታችንን በራስ አቅም የማረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን ብለዋል።

ዛሬ በእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ እና በኤኤምጂ (AMG) – እንዶዴ የባቡር መሥመር ፕሮጀክቶች ላይ ያደረጉት ምልከታ፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም በጠንካራ መሠረት ላይ እየቆመ ለመኾኑ በተግባር ያረጋገጠ መኾኑን ገልጸዋል።

የኤኤምጂ – እንዶዴ የባቡር መሥመር በሀገር በቀል የግል ኩባንያ ፋይናንስ የተደረገ የመጀመሪያው የባቡር መሠረተ ልማት ነው። ይሄም የግል ዘርፉ ለሀገር ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል። በልዩ ትኩረት ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ በመጠናቀቅ ላይ መኾኑም “ዐቅዶ መጀመር፣ ጀምሮ መፈጸም” የሚለውን መርሐችንን ያጸና ነው ብለዋል።

ይህ የሦስት ኪሎ ሜትር ባቡር መሥመር በገላን ኢንዱስትሪ ዞን የሚመረቱ ምርቶችን ቡናን ጨምሮ በቀጥታ ከባቡር መሥመሩ ጋር በማገናኘት፣ ምርቶች በፍጥነትና በተወዳዳሪ ዋጋ ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ያስችላል ነው ያሉት።

የእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ የኮንቴነር ማከማቻ ዐቅምን በአምስት እጥፍ ሲያሳድግ፤ የጭነት የማውረድና የመጫኛ ጊዜን ከ10 ሰዓት ወደ ሁለት ሰዓት ዝቅ በማድረግ የንግድ ሥርዓታችንን ያዘምናል፤ ፈጣን የሎጂስቲክስ አገልግሎትን ይፈጥራል ብለዋል።

እነዚህ በራስ ዐቅም የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነታችንን ከማሻሻል ባለፈ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ያጸናሉ ነው ያሉት። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሕ እና የዳኝነት ሥርዓቱን በማዘመን ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።
Next articleምሁራን የጥፋት መንገድን በማውገዝ ችግሮች በንግግር እና በአመክንዮ እንዲፈቱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።