የሰርኩላር ኢኮኖሚ ሞዴል ፋይዳ እና የኢትዮጵያ ተሞክሮ።

14

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምርት ሂደት እና አጠቃቀም ላይ አዲስ እሳቤን ይዞ የመጣው የሰርኩላር ኢኮኖሚ ሞዴል ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ እና የአካባቢያዊ ትሩፋት ዕድል ይዞ የመጣ ነው።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ትዕግሥት ዘላለም (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሞዴሉ ምርት ተመርቶ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውልበትን የተለመደ አሠራር የሚቀይር መኾኑን አብራርተዋል።

እንደ ዶክተር ትዕግሥት ገለጻ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ሦሥት መሠረታዊ እና አይለወጤ መርሆዎችን ይዟል።

የመጀመሪያው ጥሬ ዕቃን በተመጠነ እና በተጠና መንገድ በአግባቡ መጠቀም ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ምርቶች ለሸማቹ በድግግሞሽ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጎ በማምረት የሀብት ብክነትን መቀነስ ነው።

ሦሥተኛው እና ወሳኙ ነጥብ ደግሞ አገልግሎት የጨረሱ ምርቶች ለዳግም ምርት ግብዓትነት የሚውሉበት ሥርዓት መዘርጋት ነው።

ይህም የምርት ሂደትን ክብ በማሽከርከር የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ያስችላል።

የአውሮፓ ኅብረት በየዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ቶን በላይ ተረፈ ምርት እንደሚያስወግድ የጠቀሱት መምህርቷ ይህንን ተረፈ ምርት ወደ ኢኮኖሚው በመመለስ ምርታማነትን ለማሳደግ ኅብረቱ እስከ 2050 ሰርኩላር ኢኮኖሚን ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ለንጽጽር አቅርበዋል።

ኢትዮጵያም ይህንን ሞዴል በፖሊሲ ደረጃ ለመተግበር በጥሩ ጅምር ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኀይል ማመንጫን እና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅን እንደ ትልቅ ስኬት ጠቅሰዋል።

ሰርኩላር ኢኮኖሚ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያሳድግ እና የአካባቢ ደኅንነትን የሚያረጋግጥ መኾኑን የገለጹት ዶክተር ትዕግሥት “ሀብትን በቆጠበ መንገድ ሀገርን ሊያሻግር በሚችል መልኩ ገንዘብ መሥራት የተለየ ስጦታ ነው” ብለዋል።

በመኾኑም በዘርፉ ያሉ መሪ ተዋናዮች አመቺ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት እና የጽንሰ ሀሳቡን ምንነት ለማኅበረሰቡ በማስረዳት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ እና ዘላቂ ኢኮኖሚ ጉዞ ማሳካት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመረጃን መመርመር እና ሀሰት ከኾነ በጋራ መታገል ያስፈልጋል።
Next articleዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመምረጥ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል።