መረጃን መመርመር እና ሀሰት ከኾነ በጋራ መታገል ያስፈልጋል።

26
ባሕር ዳር: መጋቢት08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀሰተኛ መረጃን በአደባባይ ሥብሠባዎች፣ በብሮድካስት ሚዲያ፣ በሕተመት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ መንገዶች አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ማሠራጨት የተከለከለ ተግባር ነው።
በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህርት ሕይወት ዮሐንስ በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ዓ.ም ለዚህ መፍትሔ ለማበጀት የተደነገገ እንደኾነም ተናግረዋል።
ሰዎች የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳያደርጉ የሚሠራጭ፣ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ከፍ ያለ ንግግር እንደኾነም በአዋጁ ተቀምጧል ነው ያሉት መምህርት ሕይወት።
ሰዎች ተገቢ ማጣራትን ሳያደርጉ በግርድፉ ለበርካቶች ተደራሽ ስለሚኾን አጥፊነቱ ዘርፈ ብዙ ነው ባይ ናቸው። ሀገር እንድትተራመስ እና እውነት ተዛብቶ ብዙዎች እንዲጎዱ መሣሪያ ኾኖ የሚያገለግል ነውም ብለዋል። ዓለምም ይህን እያስተናገደች እንደኾነ ተንትነዋል።
ሀሰተኛ መረጃ በሀገር ሰላም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም ነው ያሉት። በተለይ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው በማድረግ በኩል ድረሻው ከፍተኛ ነው ይላሉ። መሪዎች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ኾን ተብለው የሚፈበረኩ ሀሰተኛ ወሬዎች ፈተና እንደሚኾኑም አንስተዋል መምህርት ሕይወት።
የሕዝብ ተቋማት ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቁም ያደርጋል ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ኾኖ ሳለ በሀሰተኛ መረጃ ምክንያት አመኔታው አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሙከራ ሲደረግ ይስተዋላል ሲሉም ለአብነት አንስተዋል።
ሀሰተኛ መረጃ አብሮ ለማደግ እና አብሮ ለመለወጥ ጠንቅ ነው ባይ ናቸው። ሀሰተኛ መረጃ መተማመን እንዲጠፋ እያደረገ ያለ የዘመኑ የአብሮነት ሳንካ ነው ብለዋል።
አሉባልታ አንድ እውነት እንድትቀጥን የሚያደርግ እንደኾነም ነው የተናገሩት። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ኹኔታም ሀሰተኛ መረጃ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ እየዳረገ ነው ይላሉ።
ልዕለ ኀያል ሀገር የኾነችው አሜሪካ ሳይቀር በሀሰተኛ መረጃ ትናጣለች ነው ያሉት። ብዙውን ጊዜ ሲታይ ግን የሀሰተኛ መረጃ ውጤቱ ውድመት እና ኪሳራ እንደኾነም አብራርተዋል።
እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሀገራትን ታሪክ ብንመረምር ሀሰተኛ መረጃ ከጀርባ ገፊ ኾኖ እናገኘዋለን ነው ያሉት መምህርቷ። ሁሉም ጋዜጠኛ ኾኖ እየተነተነ ባለበት በዚህ ዘመን ሀሰተኛ መረጃ ፈተና ኾኖ መቀጠሉን አስገንዝበዋል።
ይህ መኾኑም እንደ እንቁ ስናያቸው የነበሩ እሴቶች እንዲሸረሸሩ አድርጓል ብለዋል። እኔ ላውራ እንጅ እኔ ላዳምጥ የሚል በመጥፋቱ ለዘርፈ ብዙ ችግር እየዳረገ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የዘመኑ የሀሰተኛ መረጃ ወረርሽኝ መፍትሔን ይሻል። መፍትሔዎቹም ከሕዝብም፣ ከመንግሥትም የሚጠበቁ እንደኾኑ ጠቁመዋል። ሕዝቡ መረጃን እንደወረደ እንዳይወስድ የግንዛቤ ሥራዎች አብዮት መደረግ አለበት ነው ያሉት። የኢትዮጵያ የመረጃ አጠቃቀም አብዮት ያስፈልገዋልም ብለዋል።
የተግባቦት ዕውቀትን የሚያነቁ አሠራሮችን ማመቻቸት ተገቢ ነውም ይላሉ። ይህን የሚመለከታቸው ተቋማት ታች ድረስ ወርደው ማሳወቅ እንደሚጠይቅም አስረድተዋል። ሰዎች መረጃን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ማሳወቅ እና የማንቃት ሥራው ችላ መባል እንደሌለበትም አብራርተዋል።
“ነገርን አድምጦ እህልን አላምጦ” የሚለው የማኅበረሰባችን ቱባ ባሕል መሸርሸሩ ደግሞ ሁሉንም አካል ሊያስጨንቀው ይገባል ብለዋል። ሁሉም አካል መረጃን እንደወረደ ከመውሰድ ይልቅ እንዴት ብሎ የማጣራት ባሕሉን ማሳደግ መፍትሔ ነውም ይላሉ።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፉክክር እና ትብብርን በሚዛን በማየት ሀገርን በማስቀደም መንቀሳቀስ ይገባል።
Next articleየሰርኩላር ኢኮኖሚ ሞዴል ፋይዳ እና የኢትዮጵያ ተሞክሮ።